አዲስ አበባ (ኢትዮጵያ ቱ ደይ)ሚያዝያ 08 ቀን 2016
የፌዴራል ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የዉጪ ድርጅቶች በራሳቸው ስራቸውን ለማከናወን ወይም መንግስታዊ ካልሆኑ አገር በቀል ድርጅቶች ጋር የገንዘብ ፣ የዓይነት እና የእዉቀት ድጋፍ በማድረግ መስራት የሚያስችላቸውን የምዝገባና አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 986/2016 አዉጥቷል።
ለዉጪ ድርጅቶች ምዝገባና አስተዳደር የወጣዉ ይህ አዲሱ መመሪያ በቅርብ ጊዜ ከወጡት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መመሪያዎች አንደኛው መሆኑ ታዉቋል።
በሀገር ዉስጥ የሚንቀሳቀሱ ግብረሰናይ ድርጅቶች ከዚህ ቀደም
በባለስልጣኑ ፍቃድ የሚሰጣቸው ቢሆንም መመሪያ ሳይወጣላቸዉ ቀርቷል።
መመሪያው በኢትዮጵያ ዉስጥ የሚንቀሳቀሱ የዉጪ የሲቪል ማህበራት የሥራቸውን ሂደትና አፈፃፀም ለማፋጠንና ለመከታተል የሚያግዙ እንዲሁም ግልፅነት እና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያግዙ መብቶችና ግዴታዎችን አካቷል።
በኢትዮጵያ ዉስጥ የዉጪ ድርጅቶች የሚመዘግብትን እና ህጋዊ ጥቅሞቻቸው የሚጠበቅበት ሁኔታዎች ማመቻቸት እንዲሁም ህጋዊ ግዴታዎቻቸውን እንዲወሰን ማድረግ ዓላማ እንዳለዉም ካፒታል ከመመሪያው መረዳት ችሏል።