አዲስ አበባ (ኢትዮጵያ ቱደይ): የካቲት 20፤2016 ዓ.ም.)
የኢትዮጵያ መንግስት የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤን ለመዘገብ ፍቃድ ካገኘ በኃላ ከፖለቲካ ፓርቲዎችን እና ከአክቲቪስቶች ጋር በመገናኘት መረጃ ሰብሰቧል ያለዉን የፈረንሳዩ ጋዜጠኛን በቁጥጥር ስር እንዲዉል ማድረጉን አስታዉቋል።
የፈረንሳይ ዜግነት ያለው ጋዜጠኛ አንቶንዮ ጋሊንዶ የሰበሰበዉ መረጃዎቹ ለሀገሪቱ ብሄራዊ ጥቅም ስጋት በመሆናቸው ግለሰቡ ተጠርጥሮ የካቲት 14/2016 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ውሎ በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት እንደቀረበ ተነግሯል።
ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን የተነገረ ሲሆን ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ እያደረገ እንደሆነም ተሰምቷል።
ከቀናት በፊት የአፍሪካን ኢንተለጀንስ ድረገጽ ዘጋቢው አንቶንዮ ጋሊንዶ ሲቪል በለበሱ የደህንነት ሰዎች ከሆቴሉ በቁጥጥር ስር ውሎ መወሰዱን ድረገጹ አስታውቆ ነበር።
አለምአቀፉ የጋዜጠኞች ተቆርቋሪው ተቋም ሲፒጄ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋዜጠኛውን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቁት የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።
ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ ለእስር የተዳረገው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ባለስልጣን የሆነውን በቴ ኡርጌሳን ቃለመጠይቅ እያከናወነ ባለበት ግዜ መሆኑን ከጠበቃው ታምሩ ወንድምአገኘሁ ያገኘውን መረጃ ዋቢ በማድረግ ሲፒጄ አስታውቋል።