አዲስ አበባ (ኢትዮጵያ ቱደይ) የካቲት 20 ቀን 2016 ዓም:- በጋምቤላ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ በተካሄዱ ግጭቶች፤ ቢያንስ 138 ሰዎች መገደላቸውን እና በ113 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።
ዛሬ ረቡዕ የካቲት 20፤ 2016 ይፋ የተደረገው ይህ የምርመራ ሪፖርት፤ ተደጋጋሚ ግጭቶች ያስተናገደው የኢታንግ ልዩ ወረዳን ጨምሮ በጋምቤላ ወረዳ፣ በጎግ ወረዳ እና በጋምቤላ ከተማ የተከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የዳሰሰ ነው።
በጋምቤላ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በየጊዜው ለሚያገረሽው ግጭት በመነሻነት የተጠቀሰው በግንቦት 2015 ዓ.ም. በኢታንግ ልዩ ወረዳ የተፈጠረ ክስተት ነው።
በወቅቱ በልዩ ወረዳው ፒኝዋ ቀበሌ ነዋሪ የነበረ ግለሰብ “ጫካ ለእንጨት ለቀማ ሄዶ መጥፋቱን” ተከትሎ፤ በፒኝዋ እና ሌር ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ቀስ በቀስ ወደ ማህበረሰባዊ ግጭት (Inter-communal conflict) ተሸጋግሮ ጥቃቶች መድረሳቸውን ኢሰመኮ በሪፖርቱ አሰፍሯል። በእነዚህ ጥቃቶች ቢያንስ 82 ሰዎች ሲገደሉ፤ 80 የሚሆኑ ሰዎች ላይ ከቀላል እስከ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ኮሚሽኑ ገልጿል።
ከዚህ ክስተት ሁለት ወር በኋላ በልዩ ወረዳው ውስጥ በሚገኙት ሌር እና ፒኖ ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል በተከሰተ የእርስ በእርስ ግጭት ቢያንስ፤ የ46 ሰዎች ህይወት ማለፉን ኢሰመኮ አስታውቋል። በግጭቱ 46 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን እና ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ከተጎጂ ቤተሰቦች እና ከተለያዩ አካላት መረዳቱን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ጠቅሷል። ይህ ግጭት ከተካሄደ ከሳምንት በኋላ “የታጠቁ ቡድኖች” በሌር ቀበሌ ላይ ፈጽመውታል በተባለ ጥቃት፤ ቢያንስ የ19 ሰዎች ሕይወት ማለፉን እና 11 ሰዎች መቁሰላቸውን ኮሚሽኑ ባሰባሰበው መረጃ እና ማስረጃ ማረጋገጡንም በሪፖርቱ ላይ አስፍሯል።
የኢሰመኮ የምርመራ ሪፖርት፤ ከኢታንግ ልዩ ወረዳ በተጨማሪ በሰኔ እና ነሐሴ 2015 ዓ.ም. በጋምቤላ እና ጎግ ወረዳዎች የተፈጸሙ ጥቃቶችን ዝርዝር መረጃ አካትቷል። የጋምቤላ ክልል መንግስት መቀመጫ በሆነችው ጋምቤላ ከተማ፤ በግንቦት፣ ሰኔ እና ሐምሌ 2015 ዓ.ም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች በተመሳሳይ መልኩ በሪፖርቱ ቀርበዋል።