አዲስ አበባ (ኢትዮጵያ ቱደይ) የካቲት 20 ቀን 2016 ዓም :-የትግራይ ክልል የኮሚኒኬሽን ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ረዳኢ ሓለፎም የካቲት 19/2016 ዓ.ም ምሽት ለትግራይ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ ፤ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ውል ሙሉ በሙሉ ባለመተግበሩ ምክንያት የህዝብ ስቃይና ሞት መቆም አልቻለም ፤ ስለሆነም ውሉ በሙሉ እንዲተገበር የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር የፌደራል መንግስትና የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ተከታታይ ውይይቶች በማካሄድ ላይ ናቸው ብለዋል።
” ሰላማዊ ፣ ዴሞክራሲያዊና ፓለቲካዊ መንገድ በመጠቀም የትግራይ ህዝብ ጥያቁዎች እንዲመለሱ መስራት ተመራጭ አማራጭ ነው ” ያሉት አቶ ረዳኢ ይህንን ታሳቢ በማድግ በሚቀጥሉት ሳምንታት የፕሪቶሪያ የሰላም ውል ፈራሚዎች ከአደራዳሪዎች ለመወያየት መርሃ ግብር ተይዟል ብለዋል።
በትግራይ የተከሰተው ደርቅ ወለድ ረሃብና ሞት አስመልክቶ ከፌደራል መንግስት የነበሩ ልዩነቶች ወደ አንድ ማምጣት እንደተቻለ የገለፁት አቶ ረዳኢ ሓለፎም ፤ የጋራ መፍትሄ ለማበጀት በጋራ እየተሰራ መሆኑ አብራርተዋል።
ሃላፊው አያይዘው እንደገለጹት ፤ የጊዚያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ የካቲት 18 ና 19 /2016 ዓ.ም ለ2 ቀናት ባካሄደው ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎች አስተላልፏል።
ካቢኔው የኢንቨስትመንትና የኤክስፓርት መመሪያ እንዲሁም የአርበኞች ኮሚሽን አሁናዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ተሻሽሎ እንዲተገበርና እንዲቋቋም ወስኗል።
የትግራይ ህዝብ በከባድ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ ችግሮች ውስጥ እያለ ፤ በጊዚያዊ አስተዳደሩና በፀጥታ ሃይል አዛዦች ላይ እየተደረገ ያለው የተቀናጀና የተናበበ የማጥላላት ዘመቻ ያወገዘው ካቢኔው ፤ የትግራይ ህዝብና አመራሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት መንፈስ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት እንዲረባረቡ ሲል ጥሪ አቅርቧል።