አዲስ አበባ(ኢትዮጵያ ቱደይ) ጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓም
በደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ህወሓት ትናንት በትግራይ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት አባቶች አማካኝነት ሁለቱ የህወሓት ቡድኖች ያደረጉት የፊት ለፊት ግንኙነት ከብፁአን የሃይማኖት አባቶች ተግሳፅና ምክር የዘለለ ውጤት እንደሌለው ተናገረ።
የደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ህወሓት ዛሬ ምሽት አጭር መግለጫ አውጥቷል።
በዚህም ፥ ” በብፁአን አበው የተዘጋጀው ፊት ለፊት የማገናኘት መርሃ ግብር ልዩነቶች በህግ ፣ ተቋማዊ ስርዓት ማእከል በማድረግ ህዝብን ከአደጋ መታደግ በሚችል የሰለጠነ ሰላማዊ መንገድ ችግሮቻችን እንድንፈታ ያለመ የምክርና የተግሳፅ መድረክ ነበር ” ብሏል።
” መድረኩን ተከትሎ የተለያዩ ውዥንብሮች መፈጠራቸው ለመረዳት ችለናል ” ያለው በደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ህወሓት ፥ “ብፁአን አበው ላቀረቡልን ምክርና ተግሳፅ ያለን ክብር እና ድጋፍ ገልፀናል ፤ ከዚህ በዘለለ የተለያዩ አካላትና ሚዲያዎች ‘ ለእርቅ እና ሽምግልና ተስማምተዋል ‘ በማለት የሚያሰራጩት መረጃ ከእውነት የራቀ ነው ” ሲል ገልጿል።