አዲስ አበባ(ኢትዮጵያ ቱደይ) ጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓም
በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2018 ምርት የጀመረው የቱርክ ኩባንያ ቪታ ፉድ ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ ገበያ ተመሳስለው የሚገቡ የከረሜላ ምርቶች አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳሰባቸው ገልጿል።
የጤና እና የደህንነት መስፈርቶችን በማክበር በሚመረቱት ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የታይታይ ከረሜላዎች እና ሉሊ ፖፖች የሚታወቀው ቪታ በቅርቡ እነዚህን ጥብቅ መስፈርቶች የማያሟሉ ተመሳሳይ ምርቶች እየተሰራጩ እንደሆነ አስታዉቋል።
የተቋሙ የኦፕሬሽንና የገበያ ኃላፊ አቶ እዩኤል ጥበቡ እንደተናገሩት እነዚህ ያልተፈቀዱ ምርቶች ሊያስከትሉ የሚችሉትን አደጋ ጎላ አድርገው በመግለጽ በጤናና በደህንነት ላይ ጉዳት ከማሳደራቸውም በላይ በዚህ ዘርፍ የሚገኙ ሕጋዊ ባለሀብቶችን ስጋት ላይ እንደሚጥሉ አንስተዋል።
እንዲህ አይነቱ ድርጊት በቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ከውጭ የሚገቡ አምራች ድርጅቶችን ተጨማሪ ኢንቨስት ከማድረግ እንዲቆጠቡ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡ ይህም በአገሪቱ ከፍተኛ ኪሳራ ያስከትላል በማለትም ስጋታቸዉን አንፀባርቀዋል።
ቪታ ፉድ ኢንዱስትሪ ምርቶቹን ሙሉ በሙሉ በተረጋገጠና ፈቃድ ባለው ተቋም እንደሆነ እና ጥራት ካላቸው ንጥረ ነገሮች የዓለምአቀፍ ደረጃን በጠበቀ መንገድ በማምረት ላይ እንደሚገኙ ተገልፀዋል ።
የቱርክ ከረሜላ አምራች ድርጅት በኢትዮጵያ ገበያ ተመሳሳይ ምርቶች መታየታቸው እና ምርቶቹ የሚመረቱበት ቦታ ካለመታወቁ ባሻገር የሚጠቀሙት ግብአት ምንነት ያልተረጋገጠ በመሆኑ ከጤና አንጻር የአደጋ ስጋት ከመሆናቸው ባሻገር በሕጋዊ ኢንቨስተሮች ላይ በከፍተኛ ደረጃ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን አንስተዋል።