አዲስ አበባ (ኢትዮጵያ ቱደይ) መስከረም 17 ቀን 2017 ዓ.ም
በአማራ ክልል ከጊዜ ወደ ጊዜ የወባ ሕሙማን ቁጥር በአስደንጋጭ መጠን እየጨመረ ይገኛል ተባለ፤ በዚህም በየጊዜው በክልሉ ባሉ ዞኖች ሪፖርት የሚደረገው የሕሙማን ቁጥር እያሻቀበ መሆኑ ተገልጿል።
ከሐምሌ 2016 ዓ.ም ጀምሮ 415 ሺህ 173 የወባ ሕሙማን ሪፖርት መደረጉን በአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወባ መከላከል እና መቆጣጠር ፕሮግራም አሥተባባሪ ዳምጤ ላንተ ገልጸዋል፡፡
አሥተባባሪው በክልሉ በወባ ስርጭት ቀዳሚውን የሚይዘው የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር (18 ነጥብ 4 በመቶ) መሆኑን ጠቁመው ደቡብ ጎንደር ዞን (18 በመቶ)፣ ማዕከላዊ ጎንደር ዞን (11 በመቶ) የሚሆን ስርጭት ሪፖርት መደረጉን እና ቀሪዎቹ ምዕራብ ጎጃም፣ ምሥራቅ ጎጃም እና ምዕራብ ጎንደር በወባ ስርጭት በቅደም ተከተል ተቀምጠዋል ብለዋል፡፡
በክልሉ የተከሰተውን የወባ ክስተት ለመከላከል የወባ መከላከል አሥተዳደር ተቋቁሞ በየሳምንቱ የወባ መከላከል እና መቆጣጠር እየገመገመ ችግሮችም ሲያገኝ አስፈላጊውን እርምት እየወሰደ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት፡፡
በየዞኑም ለወባ ስርጭት አመቺ ናቸው የተባሉት ወረዳዎች ላይም የመከላከል ሥራው በሚደርሰው መረጃ መሠረት ክትትል እየተደረገ እና እየተገመገመ በኀላፊነት እየተሠራ ነው ሲሉ መግለጻቸውን ከአሚኮ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።