ከኦሮሚያ ክልል በግጭት ምክንያት ተፈናቅለው በደብረብርሃን የሚገኙ ዜጎች የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶች ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠየቁ።
ተፈናቃዮቹ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎች በተከሰተ ማንነትን መሰረት ያደረገ ግጭት ለደህንነታቸው ሰግተው ወደ ደብረብርሃን ከመጡ አንድ ዓመት ከ6 ወር ሆኗቸዋል።
ከምዕራብ አርሲ ዞን ብቻ 200 ዜጎች የተሻለ ደህንነት ፍለጋ ለብዙ ዓመታት ይኖሩባቸው የነበሩ ቤቶቻቸውን ለቀው በአማራ ክልል ደብረብርሃን ከተማ ተጠልለው ይገኛሉ።
ተፈናቃዮቹ በከተማዋ ባሉ የመንግስት ትምህርት ቤቶች እና ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መጠለላቸውን የኢትዮጵያ ቱዴይ ጋዜጠኛ በስፍራው ተገኝቶ ተመልክቷል።
በምዕርብ አርሲ ስር ካለችው ዶዶላ ከተማ ተፈናቅለዉ ከመጡት መካከል አንዱ የሆነው የ22 ዓመቱ በረከት ይስሀቅ በደብረብርሃን ሀይለማርያም ማሞ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መኖር ከጀመረ አንድ ዓመት አልፎታል።
“ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ተፈናቅለው ወደ ከተማዋ ከመጡ ተፈናቃዮች ጋር አንድ ላይ ተጠጋግተን እየኖርን ነው” የሚለው ወጣት በረከት ኑሯችን ለኮሮና ቫይረስ ጥቃት ያጋልጣል ሲል ስጋቱን ገልጿል።
በተለይም አዛውንት እናቴ እና አያቴም አብረውኝ በዚህ መጠለያ ውስጥ መኖራቸውን ሳስብ ጦርነት ሸሽተው ለመኖር ብለው ወደዚህ የተሰደዱ ቤተሰቦቹን የማጣት ስጋት እንደተሰማውም ወጣት በረከት ተናግሯል።
“ብዙዎቻችን በተለይም እድሜያችን ለስራ የደረስን ሰዎች በከተማዋ የተለያዩ ዕለታዊ ገንዘብ የሚያስገኙ ስራዎችን ስንሰራ ውለን ማታ እንገናኛለን” የሚለው ወጣት በረከት ሁላችንም ከዋልንበት ቫይረሱን ይዘን ልንመጣ የምንችልበት እድል ሰፊ አለ ሲልም ተናግሯል።
“በከተማዋ እድሜያቸው ለገፉ ሰዎች እና ለጤና ባለሙያዎች ክትባት እየተሰጠ ነው” የሚል ወሬ ሰምቼ እናቴ ክትባቱ እንዲሰጣት ብዙ ጥረቶችን ባደርግም ማግኘት እንዳልቻለ የተናገረው ደግሞ ሌላኛው ተፈናቃይ ወርቅነህ በቀለ ነው።
ከአንድ ዓመት በፊት ስለ ኮሮና ቫይረስ ሚዲያው እና በየቦታው ሰው ሁሉ ያወራ ነበር ትንሽ ትንሽም ቢሆን ሳኒታይር ቀበሌው እና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ይሰጡን ነበር አሁን ግን ጉዳዩ ተረስቷል የለም ሲልም ተናግሯል።
ሌላኛዋ በቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ከሁለት ልጆቿ እና ከእናቷ ጋር የምትኖረው ተፈናቃይ አይናለም ደረሰ ትባላለች።
ጋራጅ፤ ምግብ ቤት፤ ጎሚስታ እና ላቢያጆ እና ሌሎች ንብረቶቼ በሻሸመኔ ከተማ ከአንድ ዓመት በፊት በተከሰተ ብጥብጥ ሲወድምብኝ ልጆቼን እና እናቷን ለማትረፍ ባዶ እጇን ወደዚህ እንደመጣች አይናለም ትናገራለች።
የነበረኝን ንብረት ባንድ ጀንበር አጥቼ የሰው እጅ ጠበቂ በመሆኔ ማስክ እና ሌሎች ነገሮችን ማግኘት አልቻልኩም ብላለች።
“በጥይት ከመሞት ብለን ወደዚህ ብንመጣም በስንት መከራ ለዚህ ያበቃኋት እናቴን በዚህ ዘመን አመጣሽ ኮሮና ቫይረስ እንዳላጣ፤ ልጆቼንም ያለእናት እንዳላስቀር ስትልም ስጋት እንደገባት ተናግራለች።
የደብረብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ደስታ አንዳርጌ በበኩላቸው በከተማዋ ከኦሮሚያ፤ደቡብ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የተፈናቀሉ ከ5 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንዳሉ ገልጸዋል።
“የመጀመሪያው ትኩረታችን ለተፈናቃዮቹ ምግብ እና ሌሎች መሰረታዊ ድጋፎችን ማድረስ ነበር” የሚሉት አቶ ደስታ ባንድ ስፍራ ብዙ ሆነው የሚኖሩትን በእድሜ እና ከመጡበት አካባቢ አንጻር ከፍለን መፍትሄ ለመስጠት ሞክረናል” ሲሉ ተናግረዋል።
ለኮሮና ቫይረስ የከፋ ተጋላጭ የሆኑትን በተለይ በእድሜያቸው ገፋ ያሉትን ወደ ተሻለ ቦታ ብናዛውራቸውም የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ወይም ማስክ እንዲሁም ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ግን በሚገባ አላደረስንም ብለዋል።
አሁን ላይ ተፈናቃዮቹን ወደ ቀድሞ ቦታዎች የመመለሱ ስራ ስለተጀመረ ድጋፍ የሚሹት ዜጎች ቁጥር አነስተኛ ስለሆነ የኮሮና ቫይረስ ክትባትን ጨምሮ ሌሎች የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶችን ለተፈናቃዮቹ እናደርሳለን ብለዋል ምክትል ከንቲባው።
ደብረብርሃን ከተማ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ አቅጣጫ ከአዲስ አበባ 163 ኪሎ ሜተር ርቀት ላይ የምትገኝ ስትሆን በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና ከተማ ናት።
ሰኔ 16 ቀን 2013 ዐሰ.ም
አዲስ አበባ