አዲስ አበባ (ኢትዮጵያ ተደይ)መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ላይ ጉልህ ድርሻ በመያዝ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እያደረጉ የሚገኙት የቻይና ባለሃብቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያጋጠማቸው በሚገኘዉ ተግዳሮቶች ምክንያት ወደ ጎረቤት ሀገራት እየሄዱ እንደሚገኝ ነዉ ያስታወቁት።
እነዚሁ ባሀብቶች በመንግስት አመቺ የስራ ሁኔታዎች እየተሰጠ ባለመሆኑ ወደ ጎሮቤት ሃገራት ማለትም ወደ ኬንያ ፣ ኡጋንዳ እንዲሁም ታንዛኒያ እያማተሩ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።
በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ተወካይ እንደተናገሩት በብዙ ምክንያቶች ቻይናውያን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያላቸውን ንግዳቸውን ወደ ጎሮቤት አገሮች አዙረዋል ።
“ይህ ለኤምባሲው ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ትልቅ ስጋት ነዉ ምክንያቱም የእኛ ተልዕኮ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለዉን ትብብር ማመቻቸት እንደመሆኑ ይህ ደግሞ በተለይ ለኢትዮጵያ ማህበረሰብ ትልቅ ስጋት ነዉ” ብለዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና ባለሀብቶች ተወካይ በበኩላቸው እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ትልቅ ፈተና እንዳለባት አረጋግጠዋል። የመጀመሪያው የደህንነት ቀውስ፣ የጥሬ ገንዘብ እጥረት እና እንዲሁም ግብይት ስርዓት እየጠበበ መምጣቱ ዋነኛው ምክንያቶች እንደሆኑ አስረድተዋል።
ከግብር ጋር በተያያዘ ደግሞ ባለሀብቶች የሚያጋጥሟቸው ሌላኛዉ ተግዳሮት መሆኑን ያነሱ ሲሆን ሁል ጊዜ “ከጉምሩክ ቢሮ ጋር በተያያዘ የሚመጣው ቀረጥ” ከባድ አድርጎታል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ እንዳስታወቀው ቻይናውያን ባለሃብቶች በመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ኩባንያዎች በመክፈት ለራሳቸው ገንዘብ እያፈሩ ለኢትዮጵያ ዘመናዊነት ደግሞ የማይተካ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
እ.ኤ.አ. በግንቦት 2024 የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ከ2,000 በላይ ፕሮጀክቶች ላይ የተሳተፉ ሲሆን እስከ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ኢንቨስትመንት እና ወደ ከ6000 ሺህ በላይ የሚጠጉ የስራ እድሎችን መፍጠራቸው የቅርብ ጊዜ መረጃዎች ያመላክታሉ ።