አዲስ አበባ ( ኢትዮጵያ ቱደይ) መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም
91.4 ቢሊየን ብር የሚጠይቀው የመንግስት ሰራተኞች “የደሞዝ ጭማሪ” ዝርዝር ይፋ ተደርጓል፡፡
በጭማሪው 2.3 ሚሊየን የፌደራልና የክልል መንግስታት የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞች፣ 56ሺህ ተሿሚዎች፣ ለሀገር ደህንነት ሲባል ቁጥራቸው የማይቀመጠው የክልል ፖሊስ፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የመከላከያ ሰራዊት እና የፀጥታ አካላትን ጨምሮ የደሞዝ ማሻሻያው ተጠቃሚ ናቸው፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ ለዝርዝር የደሞዝ መግለጫው በፃፉት መግቢያ “… በተለይም ዝቅተኛ የደመወዝ ተከፋይ ሰራተኞች በኑሮ ውድነት እንዳይጎዱ እና ሊደርስ የሚችለውን የኑሮ ጫና በመጠኑም ቢሆን ለመቋቋም እንዲችሉ…” የሚል አገላለፅ መጠቀማቸው ጭማሪው በቂ አለመሆኑን መንግስትም እንዳመነበት ያመላክታል፡፡
በጭማሪው ዝቅተኛው የመንግስት ሰራተኛ ደመወዝ 4,760 ብር ሲሆን ቀድሞ ከነበረው 1,100ብር በመቶኛ የ332.7% ጭማሪ ተደርጎበታል፡፡
ከፍተኛው 20,468 ብር ደመወዝ በ5% ጭማሪ 21,491ብር ደርሷል፡፡ የተጠበቀው ጭማሪ ቢደረግም ከ6,000 ብር በታች የሚያገኙት ደሞዝተኞች ከአጠቃላዩ 47.9% በመቶ መሆናቸው አሁንም ቢሆን በመሪር ድህነት ውስጥ ያለው ቤተሰብ ከፍተኛ መሆኑ ይታያል፡፡
ቀሪ 41% (ደመወዛቸው 6,000-10,600 ብር የሆኑ) መደበኛ ድህነት ውስጥ ሲገኙ ገቢያቸው ከ10,556ብር በላይ የሚገኙትም ልዝብ ድህነት ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡
ይህ ልኬት በአለም አቀፍ የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ወጪዎችን እንዲሁም የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ አገልግሎት የቤተሰብ ጥናት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል ለመተመን የሀገር ኢኮኖሚ እድገትና ምርታማነት፣ የሰራተኛው ወርሃዊ ፍጆታ እንዲሁም አንድ ሰው የሚያስፈልገውን ዝቅተኛ ካሎሪ (የተመጣጠነ ምግብ ትመና) ማስላት ስለሚያስፈልግ መረጃዎቹ እስከሚጠቃለሉ ለዝቅተኛ ደሞዝ ትመና የሚጠጋጋ ማሻሻያ ማድረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ይህ የደሞዝ ማሻሻያ ከስድስት አመታት በኋላ እንደመደረጉ የመንግስት ሰራተኞች የአሁኑን የምንዛሬ ልዩነት ብቻ ሳይሆን ለአመታት እየተደመረ የመጣውን ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ይቋቋሙታል ማለት ዘበት ነው፡፡
ስለሆነም መንግስት ከደሞዝ ማሻሻያው ጎን ለጎን የገበያ ዋጋ እንዳይንር የሚያደርጉና ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ማህበረሰብ ሊደጉሙ የሚችሉ ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ መፍትሄዎችንም ሊጠቀም ያስፈልጋል፡፡