የሳምንቱ እንግዳችን ዶክተር በየነ ተክሉ ይባላሉ፡፡ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ናቸው፡፡ ትውልድና እድገታቸው ምእራብ ሸዋ ጊንጪ ከተማ ነው፡፡ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በግብርና ሳይንስ ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ እንዲሁም ሁለተኛ ድግሪያቸውን በአግሮ ፎረስተሪ ዘርፍ ከሀዋሳ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል፡፡ በአየር ንብረት ለውጥ እና በጥምር ግብርና በኔዘርላንድ ሀገር የዶክተሬት ድግሪያቸውን /ፒ.ኤች.ዲ/ ሰርተዋል፡፡
በግብርናው ዘርፍ በማስተማርና በምርምር ለ15 አመታት አገልግለዋል፡፡ 14 የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎችን ያሳተሙ ሲሆን በብዝሀ ህይወት እንዲሁም ለአየር ንብረት ለውጥ መጋለጥ በማህበረሰቡና በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ የሚሉና ሌሎችም ፕሮጀክቶች አላቸው፡፡ በአየር ንብረት ለውጥ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡ መልካም ንባብ
የአየር ንብረት ለውጥ ምንነትና የሚያስከትለውን ጉዳት ቢገልጹልን
ዶክተር በየነ፦ አለምን እያስጨነቀ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ በዋናነት የበካይ ጋዞች ወደ ከባቢ አየር መሄድ ነው፡፡ ይህም በአብዛኛው በሰው ሰራሽ ምክንያቶች የሚወጡ በካይ ጋዞች ወደ አየር ሲሄዱ የምድር መሞቅን ያስከትላል፡፡ ሙቀት ሲጨምር ብዙ ነገሮች ይቀየራሉ፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ በየአስር አመቱ ወደ 0 ነጥብ 2 ድግሪ ሙቀት እየጨመረ ነው፡፡ አንዳንዶች ከ0 ነጥብ 2 እስከ 3 ድግሪ እየጨመረ ነው ይላሉ፡፡
ሙቀት ሲጨምር ተፈጥሮ ላይ ብዙ ተጽእኖ አለው፡፡ የመጀመሪያው ተጽእኖ ሥነ ሕይወት ላይ ነው፡፡ ሙቀት በጨመረ ቁጥር እጽዋት ተስማሚ የሆነ አየር ስለሚፈልጉ ከሚበቅሉበት አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ እንዲሄዱ ያደርጋል፡፡ እጽዋትም ሆኑ የሰው ልጆች ተስማሚ አካባቢ ይፈልጋሉ፡፡ ለምሳሌ ቡና በመካከለኛ አየር ንብረት ይበቅል የነበረው አሁን ደጋ አካባቢ መብቀል ጀምሯል፡፡ ይህም ሙቀት እየጨመረ በመምጣቱ በመካከለኛ “አልትቲውድ” የምናገኘው ቡና ከ50 እና 60 አመታት በኋላ ደጋ አካባቢ ልናገኘው እንችላለን፡፡ ከዚህ አኳያ በመካከለኛ አልትቲውድ አካባቢ ያለው ማህበረሰብ የምግብ ዋስትና ላይ ተጽእኖ ያደርሳል ማለት ነው፡፡
በሰው ልጅ ላይም እንዲሁ ተጽእኖ ያደርሳል፡፡ ሙቀት ሲጨምር ጃኬት ደርበህ ከሆነ እንድታወልቅ ያስገድድሀል፡፡ ቦታ ቀይር ወይም ተስማሚ ነገር አመቻች እያለህ ነው፡፡ በሌላ በኩል የጤና ችግርም ያመጣል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጉዳት እንዴት መከላከል ይቻላል?
ዶክተር በየነ፦ እነዚህን ችግሮች በሁለት መንገድ መፍታት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው መቋቋም ወይም መላመድ ሲሆን ሌላው በካይ ጋዞችን መቀነስ ወይም መያዝ ነው፡፡ ሀገራችን በሁለቱም ላይ ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፋ እየሰራች ነው፡፡
መላመድ ስንል ሙቀቱ እየጨመረ ሲመጣ የመልመድ ሁኔታው እንዴት ይተግበር የሚለው ሥራ ተሰርቷል፡፡ ለምሳሌ÷ ለግብርና ሴክተር ለአየር ንብረት ለውጥ መረጃ መስጠት፤ ትንታኔ በመስጠት አርሶ አደሮች የሚዘሩበትን ወቅት በመረጃ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ማድረግ፡፡ ሌላው የተፋሰስ ልማት አንዱ ስትራቴጂ ነው፡፡ ይህም የአፈር ለምነት በጨመረ ቁጥር ውሃ ስለሚይዝ የተሻለ ምርት እናገኛለን፡፡ ቴክኖሎጂ መጠቀም እንዲሁም የግብርና ምርትና ምርታማትን የሚያሳድጉ ምርምሮችን በማድረግ የምግብ ዋስትናን በመጨመር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ግብርናን መተግበር ይቻላል፡፡
ምርትና ምርታማትን ለመጨመር ቴክኖሎጂ ማመንጨት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ቶሎ የሚደርሱ ሰብሎችን ማስተዋወቅ፣ ድርቅ የሚቋቋሙ ዝርያዎችን ማስፋፋት፣ ተስማሚ ዛፎችን መትከል እንዲሁም ተፋሰሶችን መስራትን ያካትታል፡፡
ሌላው “ሪሊያንስ” መጨመር ነው። በዚህም ከግብርና በተጨማሪ ንግድ እንዲነግዱ፣ ከሰብል በተጨማሪም ንብ ማነብና እንስሳት እርባታ ላይ እንዲሰማሩ ማድረግ ነው፡፡ አንድ ሰብል ላይ ብቻ ጥገኛ ከሆነ አርሶ አደሩ በቀላሉ ሊጠቃ ይችላል፡፡
አዳፕቴሽን /ማላመድ/ የአየር ንብረት ለውጡን ለማስቆም ማላመድ አለብን፡፡ ከማዳበሪያ ይልቅ ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያ /ኮምፖስት/ መሻገር ነው፡፡ ማዳበሪያ የሚሰራልን የአፈር ውስጥ ካርቦን እስካለ ድረስ ነው፡፡ ወደ ኮምፖስት ስንሄድ የአፈሩን ለምነት እንጨምራለን፡፡ ለምነት ጨመረ ማለት ውሃ ይይዝልናል፡፡ ምርታማም፣ ጤናማ መሆን ይቻላል፡፡
ሌላው መስኖ ነው፡፡ ዝናብ እኩል ስርጭት ስለማይኖረው መስኖ ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ “ሪስትሪክሽን” የተጎዱ መሬቶችን እንዲያገግሙ በማድረግ ምርት እንዲሰጡ ያደርጋል፡፡ እንዲሁም በካይ ጋዝን ይይዝልናል፡፡ እነዚህን ስንተገብር መቋቋም እንችላለን፡፡
ሁለተኛው ሜቲኬሽን ሲሆን ይህም በካይ ጋዞች ወደ አየር ንብረት ለውጥ እንዳይሄድ መያዝ ማለት ነው፡፡ አብዛኛውን የሚይዘው ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ነው፡፡ “ሚቴን” የሚባልም አለ፡፡ በዋናነት ግን ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ስለሆነ ዛፎችን ስንተክል ካርበንን ይይዙልናል፡፡ ስለዚህ ብዙ በተከልን ቁጥር ወደ ከባቢ አየር የሚሄደውን በካይ ጋዝ እንቀንሳለን፡፡ በየአመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዛፍ የመትከል ሥራ የሚተገበረው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
ለሙቀት መጨመር በዋናነት የሚጠቀሱት ምንድናቸው?
ዶክተር በየነ፦ “ግሪን ሀውስ ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ” ከ40 በመቶ በላይ ይይዛል፡፡ “ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ” በብዛት ከመኪናዎች፣ ከኢንዱስትሪዎች “ፎሲል ፊውል” ስናቃጥል የሚወጡ ናቸው፡፡ እነዚህ ከባቢ አየር ላይ ሲሄዱ እንደ “ግሪን ሀውስ ሰርፌስ” ይሰራል። ስለዚህ ከምድር የሚሄደው ሙቀት ወደ ላይ እንዳይሄድ በማድረግ ወደ ታች ይመልሱታል ማለት ነው፡፡ ይህ ሲሆን ምድር ትሞቃለች። ስለዚህ እነዚህን በካይ ጋዞች ስንቀንስ የምድርን ሙቀት መጠን እየቀነስን ነው ማለት ነው፡፡
አሁን የአለም ሙቀት ከ2 ድግሪ እንዳይበልጥ ነው የምንሰራው፡፡ ከ2 ድግሪ በላይ ከጨመረ የተለያዩ ችግሮችን ያስከትላል፡ ፡ ለምሳሌ በሰውነታችን ላይ ያሉ ኢንዛይሞች የሚሰሩት በተወሰነ ሙቀት ሲሆን ከዚያ በላይ ሲሆን ዲኔቸር ይሆናል፡፡ ከዚያም የሰው ልጆች ጤና ላይ ችግር ያመጣል፡፡ እንደ ካንሰርና ሌሎች ይህን ተከትሎ የሚመጡ በሽታዎች ይበዛሉ፡፡ ለዚህ ነው የአየር ንብረት ለውጥ ላይ በትኩረት መስራት ያስፈለገው፡፡
ሙቀት ሲጨምር በተለይ በረዶ እና ትላልቅ የውሃ አካላት አካባቢ በሙቀት ሳቢያ በረዶ ሲቀልጥ ጎርፍ ይከሰታል፡፡ ያልተጠበቀ ሀይለኛ ዝናብ ያስከትላል፡፡ በኛ ሀገርም በቅርቡ እየተከሰቱ ያሉ የመሬት መንሸራተቶች የዚሁ ውጤት ናቸው፡፡ ከምንጠብቀው በላይ ዝናብ ሲዘንብ እንደ አፈሩና ምድራዊ አፈጣጠር ሁኔታ ዝናቡ መሬት ሰርስሮ ይገባል፡፡ ይህም መሬቱን ሊከፍለው ይችላል። የዝናቡ መጠን ሲጨምር ወደ ስር የገባው ውሀ መሬቱን ያላቅቀዋል፡፡ ይህም የመሬት መንሸራተት በማስከተል ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል፡፡
ሌላው ከፍተኛ ሙቀት ሲሆን ከመሬት የሚተነው የውሀ መጠን ይጨምራል፡፡ ይህ ደግሞ ሰብሎች በቂ ውሀ እንዳያገኙ ያደርጋል።
የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚሰሩ ሥራዎች በቂ ናቸው ብለው ያምናሉ?
ዶክተር በየነ፦ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እንደ ሀገር ብቻ ቢሰራ ያን ያህል ተጽእኖ ላናመጣ እንችላለን፡፡ እንደ አለም ነው መሰራት ያለበት፡፡
እጽዋትን ብቻ መትከል የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ አስተዋጽኦ በቂ አይደለም፡፡ አለም በሙሉ በዛፍ ተሸፍና የ”ፎሲል ፊውል” /ነዳጅ/ የምንለው አጠቃቀም ካልቀነስን ዞሮ ዞሮ ያው ነው፡፡ ለዚህም ነው የአለም “የኢንተር ገቨርመንታል ፓናል” በየአመቱ የሚካሄደው፡፡ ባለፈው በግብጽ ተካሄዶ ነበር፡፡ እዛ ላይ ነበር “ሎስ ኤንድ ዳሜጅ ፈንድ” የሚል ሀሳብ ያመጡት፡፡ ለምሳሌ ሀገራችንን በደን ብንሸፍንም አሜሪካ ወይም አውሮፓ ካልተባበረ አንተርፍም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ድሃ ሀገራት ለበካይ ጋዞች ያላቸው አስተዋጽኦ ትንሽ ስለሆነ ለተጎዱት ማካካሻ ለመስጠት የተጀመረ ነው፡፡
የአለም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ ርብርብ እየተደረገ ያለበት ምክንያት አንዱ አካባቢ የተከሰተው ችግር ሌላውን ስለማይተው ነው፡፡ ሁሉም አጀንዳ ያደረገው ማለት ነው፡፡
ኢትዮጵያ የተስማማችው “ናሽናል ኮንትሩብሽን” ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ የየሀገራቱን አስተዋጽኦ ስለሚፈለግ እያንዳንዱ ሀገር ካርበን የቀነሰበትን መንገድ ሪፖርት ያደርጋል፡፡ ሀገራችንም ከተለያዩ ሴክተሮች ውጤቱን በማጥናት ሪፖርት ታደርጋለች፡፡ በተጨማሪም እንዴት እንደምንቀንስ ስትራቴጂ በማውጣት በረጅም ጊዜ በዲካርቦናይዜሽን /ማእቀፍ/ ይተገበራል። ለምሳሌ ጥምር ግብርና ማካሄድ፣ ጸረ አረም መድሀኒት መቀነስ የመሳሰሉት መተግበር፡፡
ሌላው ለኢንዱስትሪው ታዳሽ ኃይልን መጠቀም፡፡ ታዳሽ ኃይል ለካርበን ቅነሳ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ሪፖርት ይደረጋል፡፡ ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ኤሌክትሪክ በመሸጥ “ዲካርቦናይዜሽን” እንዲቆጠርላት ታደርጋለች፡፡ ስለዚህ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ጊቤ 3 እና ሌሎችም መስፋፋታቸው አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው፡፡
ከኢንዱስትሪና ከተሽከርካሪ አንፃር የሚጠቀሙትን ነዳጅ ለመቀነስ የኤሌክትሪክ መኪና መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም ግን ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ለመቀነስ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
ሀገራችን ችግሩን ለመቆጣጠር ከምትሰራው አንፃር ያለዎት አስተያየት ምንድነው?
ዶክተር በየነ፦ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ከሚሰሩ ሥራዎች ውስጥ በግብርና፣ በኢንዱስትሪውና በታዳሽ ሀይል የሚሰሩ ስራዎች ማየት አለብን፡፡ እንደኔ በታዳሽ ሀይል በጣም ጥሩ እየተሰራ ነው፡፡ በግብርናው ትንሽ ይቀራል፡፡ ምክንያቱም ማዳበሪያ በተፈጥሮ ኮምፖስት መተካት ቢቻል ይበልጥ ምርትና ምርታማነት መጨመር እንችላለን፡፡
ኢንዱስትሪው በሀገራችን እያደገ ያለ ዘርፍ ሲሆን ታዳሽ ሀይልን ስለምንጠቀም የተሻለ ነው፡፡ ነዳጅን በኤሌክትሪክ የመተካት ሥራ ግን ጅማሮ ላይ ነን የሚል እምነት አለኝ።
አረንጓዴ አሻራ አበርክቶው ምንድነው?
ዶክተር በየነ፦ መንግስት የደን ልማትን የህልውና ጉዳይ አድርጎ መስራቱ እድል ነው፡፡ ይህን እድል በመጠቀም መስራት ይኖርብናል። ነገር ግን የተጠናና የምንቆጣጠርበት መንገድ መዘርጋት አለበት፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳቱ ከማንም በላይ ስለሚደርስብን ዛፎችን ለመትከል መረባረብ ይኖርብናል፡፡
ዛፎች በዋናነት ካርቦንን ወይም በካይ ጋዝን እንድንይዝ ያደርጋል፡፡ በኢኮኖሚው ረገድም ብዙ በተከልን ቁጥር የውጪ ምንዛሪ ያስገኝልናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ማይክሮ ክላይሜት ወይም የአካባቢን አየር ንብረት ይቀይረዋል፡፡ ይህም ሰዎች ተስማሚ መኖሪያ እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ መኖሪያ ጤናማ ከሆነ መስተጋብሩ ይጨምራል ማለት ነው፡፡ በዚህም የመስራት አቅም ይጨምራል፡፡ እንደ ሀገር የእኔነት ስሜት በመፍጠር ዜጎች ለአንድ አላማ ይሰማራሉ፡፡ በተጨማሪም አዲሱን ትውልድ ያስተምራል፣ የእውቀት ሽግግር እና የሥራ እድልም ይፈጠራል፡፡
ተጨማሪ ሀሳብ ካለዎት እድሉን ልስጥዎት
ዶክተር በየነ፦ የአየር ንብረት ለውጥ የእያንዳንዳችንን አስተዋጽኦ ይፈልጋል። ለዚህም ነው አንዳንድ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች ስለ አየር ንብረት ለውጥ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የሚታየው፡፡ ከዚህ አኳያ ሁሉም የሚመለከተው ጉዳይ በመሆኑ አስተዋጽኦው ሊቀጥል ይገባል፡፡ ሌላው የተተከለውን ችግኝ በመንከባከብ የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አንድ ዛፍ ሲቆረጥ ሁለትና ከዚያ በላይ በመተካት የራሳችንን ሀላፊነት መወጣት ይኖርብናል፡፡
አሁን አሁን በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የጠፉ በሽታዎች መልካቸውን ቀይረው ሲመጡ ይታያል፡፡ ኮቪድ፣ እንዲሁም ከሰሞኑ የታየው የዝንጀሮ ፈንጣጣ የመሳሰሉት የዚህ ችግር መነሻ ነው፡፡ ስለዚህ የአየር ንብረት ለውጥ ከየት በኩል እንደሚያጠቃን ስለማናውቅ ሁላችንም የቻልነውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለብን ይሰማኛል፡፡