ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴው የግድቡን 2ኛ ዙር ውኃ መሙላት ጀመረ።
ግድቡ ባለፈው አመት ሙሌት 4.9 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ መያዙ ይታወሳል።
የግብጽ መንግስት ኢትዮጵያ 2ኛው ዙር የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት መጀመሯን በደብዳቤ እንዳሳወቀች ገልጿል።
ሚኒስትሩ መሐመድ አብደል አቲ ኢትዮጵያ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት መጀመሯን ለግብጽ ማሳወቋን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የታላቁ ሕዳሴ ግድቡ ውኃ ሙሌት መጀመሩን የሚገልፅ ደብዳቤ ከአዲስ አበባ እንደተላከላቸው መግለጻቸውን ዘገባው ገልጿል።
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ሃምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ በቀጣናው የታየው ወቅታዊ የዝናብ እና የፈሰስ መጠን መጨመር ግድቡን ለመሙላት ሁኔታዎችን አመቺ አድርጓቸው እንደነበር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
በዚያም የተነሳ 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ የመያዙ ስራ ሃምሌ 15 ቀን መጠናቀቁ ይፋ ከሆነ በኋላ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር ሙሌት 2013 ዓ.ም ክረምት ላይ እንደምትጀምር ገልጻ ነበር፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በመጨው ሃሙስ በኢትጵያ ህሳሴ ግድብ ላይ ውይይት ያደርጋል ተብሏል፡፡
የግብጽና ሱዳን ባለስልጣናት ስብሰባውን ለመካፈል ወደ አሜሪካ ኒዮርክ አስቀድመው ያቀኑ ሲሆን ኢትዮጵያ በበኩሏ በግድቡ ዙሪያ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ከሚደረገው ድርድር ውጭ የሌላ አካላት ጣልቃገብነት እንደማትቀበል በተደጋጋሚ አስታውቃለች፡፡
እንዲሁም ኢትዮጵያ የአረብ ሊግ እና ሌሎች አገራትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ተቀባይነት የለውም በሚል በተደጋጋሚ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል በማሳወቅ ላይ ትገኛለች።
ሰኔ 29 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ