ዳዊት አስታጥቄ
በብራስልስ ቤልጂየም መቀመጫውን ያደረገው ፑራቶስ የተባለው የኬክ፣ የዳቦና የቸኮሌት ግብዓት አምራች በአዲስ አበባ ያስገነባውን ፋብሪካና ልዩ የምግብ የፈጠራ ማዕከል አስመረቀ። ወሎ ሰፈር አካባቢ የተገነባው ይህ በዓይነቱ ልዩ የፈጠራ ማዕከል ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ እንደወጣበት ተጠቅሷል፡፡
በምርቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ በዓለም ከ100 ሃገራት በላይ ቅርንጫፎች እንዳሉት የተገለጸው ፑረቶስ የኢትዮጵያን ገበያ መቀላቀሉ የፈጠረባቸውን ደስታ የገለጹት የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኤድዋርድ ፖ “አዲሱ ፋብሪካ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት የፈጠራ ማዕከል እያደገ የመጣውን የደንበኞቻቸውን የጥራት ፍላጎት ለማሟላት ቁልፍ መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም “ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ውስጥ ያለንን ተደራሽነት በማሳደግ የኢትዮጵያን ገበያ መቀላቀል በመቻላችን ከፍተኛ ኩራት ይሰማናል፤ ሁሌም ፈጠራ ፣ ምርምር እና ልማት ላይ መዋዕለ ንዋያችንን ኢንቨስት እያደረግን እንደምንቀጥል ላረጋግጥላችሁ እወዳለው” ብለዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1919 ዓ.ም. ቤልጂየም ብራስልስ ውስጥ የተቋቋመው ፑራቶስ ለዳቦ፣ ኬክና እና ቸኮሌት ኢንዱስትሪ የተሟላ የፈጠራ ምርቶችን፣ ጥሬ ዕቃዎችንና አዳዲስ አሰራሮችን እያስተዋወቀ ያለ አንጋፋ ኩባንያ ነው፡፡ ተቋሙ በዓለም ዙሪያ ከአንድ መቶ በሚበልጡ ሃገራት ውስጥ ቅርንጫፍ ያለው ሲሆን አፍሪካ ውስጥም ኬንያ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካና አይቮሪ ኮስት ውስጥ በመሥራት ላይ ይገኛል።
ፑራቶስ–ኢትዮጵያ ሃገር ውስጥ ላሉ ኬክና ዳቦ አምራቾች፣ ዓለም ዓቀፍ ሆቴሎች፣ ሱፐር ማርኬቶች እና ሬስቶራንቶች ዓለም ዓቀፍ ጥራታችን የጠበቁ የኬክና የዳቦ ግብዓቶች ያቀርባል በተጨማሪም ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሥልጠናም ይሰጣል የተባለ ሲሆን ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ለጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ ምርቶቹን የማቅረብ ዕቅድ እንዳለው ተነግሯል፡፡
የፑራቶስ-ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዜኮ ቃሲም በበኩላቸው ለፈጠራ ያለን ፍላጎት፣ በኩርነታችን እንዲሁም ዐቢይ እሴቶቻችን ሁሌም ለጥሩ ምግብ ያለንን ተነሳሽነት ለደንበኞቻችን ለማጋራት በምናደርገው ጥረት ብርታት ይሆነናል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው ይህ ማዕከል የኩባያው ደንበኞች ችሎታቸውን እሚያዳብሩበት፣ የፈጠራ ችሎታቸውን የሚያሳድጉበትና ሀሳቦቻቸውን ወደ ተጨባጭ ፣ የተዘጋጁ ጣፋጭ ምግቦች የሚለውጡበት ልዩ ሥፍራ ይሆናል ተብሏል።