አዲስ አበባ ( ኢትዮጵያ ቱደይ) ሰኔ 2 ቀን 2016 ዓ.ም፦ በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየውን የአየር ብክለት መቆጣጠርና መከላከል ካልተቻለ፣ በ2017 ዓ.ም. እስከ 2,700 ሰዎች እንደሚሞቱ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
በባለሥልጣኑ ጥናት መሠረት እስከ 2025 ዓ.ም. ድረስ ምንም ዓይነት የመከላከል ሥራ ካልተሠራ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር 6,000 እንደሚደርስ ተገልጿል። ለብክለቱ መጨመር ዋና ምክንያት ከተሽከርካሪዎች የሚወጣ በካይ ጭስ ነው ተብሏል።
የተሽከርካሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ ሲገለፅ ከተሽከርካሪዎች መካከል አብዛኞቹ ያረጁ በመሆናቸው በዚህም የተነሳ በሰዎች ጤናና በአገር ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ሪፖርተር በዘገባው አመልክቷል።
ለከተማዋ የአየር ብክለት ተሽከርካሪዎች 28 በመቶ፣ ባዮማስ ነዳጅ 18.3 በመቶና የአፈር አቧራ 17.4 በመቶ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ሲገለፅ ይህንንም ለመከላከል የተሽከርካሪ በካይ ጋዝ የቁጥጥርና ክትትል መመርያ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷልም ነው የተባለው።
መመርያው ከተሽከርካሪዎች የሚወጣውን የጭስ ብክለት ልቀት መጠን በመቀነስ፣ የሕዝብ ጤንነት ማስጠበቅና የአየር ብክለትን መከላከልና መቀነስ እንደሚያስችል ተጠቁሟል።