አዲስ አበባ( ኢትዮጵያ ቱዳይ) ግንቦት 15፣ 2016 ዓ.ም፦ ኢትዮጵያ ውስጥ በተቀናጀ ሚዲያ፣ መረጃ አቅርቦትና ትንተና እንዲሁም ማማከር ከተሰማሩ ተጠቃሽ ድርጅቶች አንዱ የሆነው ሸጋ፣ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት (Digital Finance Service – DFS) የኢትዮጵያ (DFS Ethiopia Hub) ፕላትፎርም መከፈቱን በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል።
ይህም በኢትዮጵያ ለሚገኘው የፋይናንስ ዘርፍ አጠቃላይ መረጃ (data)፣ ምልከታና (insights and analysis) ልዩ ልዩ ግብዓቶችን ያለምንም ክፍያ የሚያቀርብ ፈጠራ የታከለበት ፕላትፎርም እንዲሆን የታለመ ነው።
ፕላትፎርሙ በሸጋ የበለፀገ ሲሆን፣ የሦስት ዓመት “አኮፋዳ” የተሰኘ ፕሮጀክት አካል ነው። በእንግሊዝኛው ምሕጻረ ቃል “አኮፋዳ” (AKOFADA – Advancing Knowledge on Financial Accessibility and DFS Adoption) የፋይናንስ ተደራሽነትንና የፋይናንስ አገልግሎት መለመድን አስመልክቶ ዕውቀትን ማስፋፋት የሚል ትርጉም የያዘ ነው። የፕሮጀክቱ ዓላማ የባለ ድርሻ አካላትን ዕውቀት በማዳበር፣ ለአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች የሚሆኑ አገልግሎቶችን መደገፍ፣ እንዲሁም በዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች ላይ ሰዎች ያላቸውን መተማመን በመገንባት የፋይናንስ ተካታችነትን ለማሻሻል ያለመ ነው።
የፕላትፎርሙ ማብሰሪያ ሥነ ሥርዐት ዛሬ በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የዘርፉ ባለሙያዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት ተከናውኗል።
የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት የኢትዮጵያ ማዕከል መከፈት፣ ሁሉን አቀፍ መረጃዎችና ምልከታዎችን በማቅረብ የግለሰቦችና ቢዝነሶችን አቅም ለመጨመር ሸጋ ይዞት የተነሣውን ተልዕኮ አንድ ጉልህ እርምጃ ወደ ፊት የሚያራምድ ነው። ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂን እና ጥራቱን የጠበቀ መረጃና ይዘትን በመጠቀም፣ ፕላትፎርሙ ዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎቶችን የምናይበትንና የምንጠቀምበትን መንገድ እንደ አዲስ ለማቅረብ ቆርጦ የተነሣ ነው። አያይዞም በተሻለ መጠን መረጃ መር ውሳኔ ሰጪነትን ለማቀላጠፍ፣ እንዲሁም በገጠርና አገልግሎቱ ባልተስፋፋባቸው አካባቢዎች የፋይናንስ ተካታችነትን በጥልቀት ለመደገፍ የሚያስችል ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት በ2025 እ.ኤ.አ ከአገሪቱ አዋቂ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ሕዝብ 70 ከመቶው የፋይናንስ አገልግሎት ውስጥ ተካታች እንዲሆን፣ እንዲሁም ክፍያዎችን ለመፈጸምና ለመገበያየት ዲጂታል አካውንት አዘውትሮ እንዲጠቀም ግብ ሰንቋል።
“አኮፋዳ” ለዚህ ግብ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
የማብሰሪያ ሥነ ሥርዐቱ፣ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት የኢትዮጵያ ማዕከል ያሉት ልዩ ገጽታዎች ለተሳታፊዎች የቀረቡበት ሲሆን፣ ለአጠቃቀም ምቹ መሆኑ እንዲሁም ከፍተኛ የትንተና አቅም እንዳለው የታየበት ነው። የሥነ ሥርዐቱ ተሳታፊዎች ከሸጋ ባለሙያዎች ጋር ሐሳብ ለመለዋወጥ ባገኙት ዕድል፣ “አኮፋዳ” እንዴት የፋይናንስ ተካታችነትንና ዕድገትን ሊያቀላጥፍ እንደሚችል ይበልጥ ለመረዳት ችለዋል።
የሸጋ ኢንሳይትስ (Shega Insights) ማናጀር የሆኑት አቶ ናትናኤል ጸጋው፣ “የፋይናንስ ተደራሽነት እና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት በኢትዮጵያ እንዲለመዱ ለማገዝ ያለንን ቁርጠኝነት ማሳያ የሆነውን ይህንን ፕላትፎርም ይዘን በመምጣታችን ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል” ሲሉ በሥነ ሥርዐቱ ላይ ተናግረዋል።
በተጨማሪም፣ “ይህ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት የኢትዮጵያ ፕላትፎርም፣ ያለሟቋረጥ የሚለዋወጠውን የዲጂታል ፋይናንስ ዓለም ተጠቃሚዎች ያለ ስጋት እንዲዳስሱና እንዲጠቀሙ የሚያስችል ነው” በማለት ገልጸዋል።
የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት የኢትዮጵያ ማዕከል የሚከተሉትን ቁልፍ ገጽታዎች የያዘ ነው:
ሁሉን አቀፍ መረጃ አቅርቦት: ሰፊ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት እና ተያያዥ መረጃዎችን (data) በማቅረብ ተጠቃሚዎች ስልታዊ ውሳኔዎች ላይ እንዲደርሱ ማገዝ።
ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ምልከታዎች: በድርጅቱ ባለሙያዎች የተዘጋጁ ኦርጂናል ዐጫጭር ጽሑፎች፣ የተዛማጅ ነባራዊ ሁኔታ ጥናቶች (case studies) እንዲሁም ሪፖርቶችን በማቅረብ፣ ዘርፉ ውስጥ ለሚገኙ ባለ ድርሻ አካላት የአገሪቱን ሁኔታ ያገናዘቡ ምልከታዎችን መስጠት እና የኢትዮጵያን ዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት በውል እንዲረዱ ማስቻል
የጠቃሚ ግብዓቶች መገኛ ማዕከል: ከዘርፉ ጋር ተያያዥነት ያላቸውና የተመረጡ የዜና ዘገባዎችን፣ ሪፖርቶችን፣ ምዘናዎችን እንዲሁም የኢትዮጵያ ዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎትን የሚያብራሩ ልዩ ልዩ ግብዓቶችን አጠቃልሎ የያዘ በቀላሉ ተደራሽ የሆነ የመረጃ ምንጭ ማቅረብ
የማብሰሪያ ሥነ ሥርዓቱ የፓናል ውይይትንም ያካተተ ሲሆን፣ በፓናል ውይይቱ ላይም በፋይናንስ አገልግሎት አቅርቦት ላይ መረጃ መር የሆነ ውሳኔ አሰጣጥ፣ ለዘርፉ የሚሆን መገልገያ አዘገጃጀት፣ እንዲሁም የፋይናንስ ተካታችነት ተዳስሰዋል። የፓናል ውይይት ተሳታፊዎቹ፣ ከፕላትፎርሙ ጋር ተዛማጅ ናቸው ያሏቸውን ምልከታዎችና ልምዶቻቸውን ያጋሩ ሲሆን፣ ፕላትፎርሙ በዘርፉ ከፍተኛ የሆነ እመርታ እንዲመጣ ለማስቻል አቅም ያለው መሆኑን አስምረውበታል።