አዲስ አበባ (ኢትዮጵያ ቱደይ) ህዳር 3 ቀን 2017 ዓም
ማንኛውም ሰው የህዝብ መገልገያ የሆኑ የተጠናቀቁ ህንፃዎች አገልግሎት ላይ ከማዋላቸው በፊት የህንጻ መጠቀሚያ ፈቃድ ማግኘት እንዳለባቸው የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሕንፃ ረቂቅ አዋጅ ማሻሻያ ላይ ከባለድርሻ አካላት ዉይይት ማድረጋቸው ተሰምቷል።
የሚኒስቴሩ የኮንስትራክሽንና መሰረተ ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ መዲና አህመድ እንደተናገሩት በነባሩ ህግ በአፈጻጸም የተለዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ፣ የአካል ጉዳተኞች ተደራሽነትን፣የግንባታ ጥራትና የሀብት ብክነት ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችል ግልጽና ለአተገባበር ምቹ የሆነ የአሰራር ስርአት መዘርጋት ተገቢ ሆኖ መገኘቱን አስረድተዋል።
በዚህም ማንኛውም ሰው አዲስ ግንባታ ለማከናወን፣ ነባር ህንፃ ለማሻሻል ፣ለማስፋፋት ወይም ለማፍረስ እንዲሁም የአገልግሎት ለውጥ ለማድረግ በቅድሚያ ተገቢውን የግንባታ ፈቃድ ማግኘት እንዳለበት አሳስበዋል።
ይህን እና ሌሎች ጥብቅ መመሪያዎችን ይዟል የተባለው አዲሱ የአዋጁ ማሻሻያ ጥናት ላይ የተመሰረተ እና ዘርፉ የደረሰበትን ደረጃ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተጠቁመዋል።