አዲስ አበባ (ኢትዮጵያ ቱደይ) ሐምሎ l 8 ቀን 2016 ዓ.ም
የፌደራል መንግስቱ ከሚያወጣው ታክስ ዉጪ ክልሎች የራሳቸዉን ህግ በማዉጣት የኮቴ በሚል በአንድ የጭነት ተሽከርካሪ ላይ ከ 90 ሺህ ብር በላይ እያስከፈሉ መሆኑን ግዙፉ የለስላሳ መጠጥ አምራች ኢንዱስትሪ የሆነዉ ኮካ ኮላ አስታውቋል ።
በኢትዮጵያ መንቀሳቀስ ከጀመረ ከ 60 ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረ የሚነገርለት ኩባንያው መንግስት በተለያዩ ጊዜያት ከሚያወጣው የህግ ማዕቀፍ ዉጪ ክልሎች በተለምዶ የነበረዉን አሰራር ወደ ህጋዊ በማምጣት ከዚህ ቀደም በአንድ ተሽከርካሪ የጭነት መኪና በአማካይ 5 ሺህ ብር የነበረዉ አሁን ግን ከ 90 ሺህ ብር በላይ እንዲሆን ተደርጓል ብሏል።
በኮካ ኮላ ቤቨሬጅ አፍሪካ በኢትዮጵያ የሕግ ኮሙዩኒኬሽ ዳይሬክተር አቶ ንጉሡ ዓለሙ በተለይ ለካፒታል እንደተናገሩት በኦሮሚያ ክልል በተለምዶ የነበረዉ የኮቴ ታክስ አሁን ግን በህግ ደረጃ ወጥቶ ተግባራዊ መደረጉን በመግለፅ በፊት በአማካይ 5 ሺህ ብር ሲያስከፍሉ የነበረዉን በመተዉ በአጠቃላይ በጭነት ተሽከርካሪ ከ 90 ሺህ ብር በላይ እንዲከፍሉ መደረጋቸውን አስረድተዋል ።
ይህ ማለት በእያንዳንዱ ጠርሙስ 1 ብር ከ 50 ሳንቲም እንደመጨመር ያህል እንደሆነ የሚያብራሩት አቶ ንጉሡ ነገር ግን እኛም የገበያዉ ዋጋ በምርቶቹ ላይ ጭማሪ እንድናድርግ አያደርግም በማለት የሁኔታውን ዉስብስብነት አብራርተዋል ።
መንግስት የኤክሳይዝ እና የተጨማሪ እሴት ታክስን ጨምሮ ሌሎች መመሪያዎችን የሚያወጣውን ተግባራዊ እያደረግን ብንገኝም በዲስትሪክት ደረጃ አንድ አንድ ከተሞች መኪናዎቻችን በሚያልፍባቸው ቦታዎች ላይ ከፍተኛ ታክስ እየተጣለበት እንደሚገኝ ገልጿል ።
ምርቶቹን በሀገሪቱ በሚገኙ በሁሉም አቅጣጫዎች የሚያሰራጭበት ከ 400 በላይ ተሽከርካሪዎች እንዳሉት የሚናገረዉ ድርጅቱ በየከተሞች በሚገኙ ኬላዎች ላይ የሚጣዉ ታክስ መሳይ ህጎች ኢንዱስትሪውን እንዲቀጭጭ የሚያደርገዉ እንደሆነ ገልጿል።
ይሄን ጉዳይ ሰሚ አላገኘም የሚለዉ ኮካኮላ በፌዴራል ደረጃ ምን እየተሰራ እንደሚገኝ ወደታች ወርዶ ጠያቄ አካል የለም ሲሉ ተናግረዋል ።