በ፦ ዳዊት አስታጥቄ
አዲስ አበባ (የኢትዮጵያ ቱደይ) ሐምሌ 7 ቀን 2016ዓ.ም
ኢትዮጵያ ዩኒቨርሳል የዉሃ አቅርቦትን ማሳካት ካለመቻሏ በተጨማሪ የኢንቨስትመንት ወጪን መመለስ አልቻለችም ተብሏል።
ይህ የተነገረዉ 12ኛዉ የባለብዙ ባለድርሻ አካላት ፎረም በመጠጥ ዉሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን ዘርፍ መድረክ ላይ ነዉ።
ላለፉት 18 ዓመታት ሲካሄድ የቆየዉ ይህ የባለድርሻ ፎረም በኮሮኖ ወረረሽኝ እና በሌሎች ምክንያቶች ተቋርጦ የቆየ ቢሆንም ከሁለት ዓመታት ወዲህ ግን በድጋሚ መሄድ እንደጀመረ ነዉ የተገለፀው ።
በዚሁ መድረክ ላይ እንደተሰማው ሀገሪቷ ዩኒቨርሳል የዉሃ አቅርቦት ማሳካት አለመቻሉ እንዲሁም የኢንቨስትመንት ወጪን የመመለስ አቅም ዉስንነት መኖሩ ሲሆን ለዚህም እንደምክንያት ከተቀመጡት መካከል የፋይናንስ አቅርቦት አለመኖር እና መሰረት ልማቶች በበቂ ሁኔታ አለመሟላት ይገኙበታል ።
የሳኒቴሽን ዘርፍ በመንግሥት አስተዳደር ዉስጥ በሁሉም ደረጃ አለመደራጀቱ ለዘርፉ ተግዳሮት እንዲሆን ማድረጉ ተሰምቷል ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዉሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሀብታሙ ኢተፋ ከልማት አጋር ድርጅቶች ጋር ባደረጉት የዉይይት መድረክ ላይ እንደተናገሩት በሀገሪቱ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎች በተለያዩ የኃይል አማራጭ ቴክኖሎጂዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ለማስፋት ትኩረት ተደርጓል ያሉት ኢንጅነር ሀብታሙ አሁን ላይ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎች በተለያዩ የኃይል አማራጭ ቴክኖሎጂዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።