አዲስ አበባ(ኢትዮጵያ ቱደይ)ሰኔ 16 ቀን 2016 ፦ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ልኬት አሁን ያለበት ሁኔታ በዓለም አቀፍ መስፈርት መሰረት መከናወኑን የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም ገለጹ፡፡
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተሰራው ስራ ግን በ2011 ዓ.ም ከነበረበት 17 ነጥብ 2 በመቶ አሁን ላይ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም፤ የኢትዮጵያ የደን ልማት ዓለም አቀፍ ልምድ ካላቸው ተቋማት ጋር በመሆን አሁን ያለበት ሁኔታ መጠናቱን ተናግረዋል።
በጥናቱ አለም አቀፍ የደን ምርምር ማዕከል፣ ሴንተር ፎር ትሮፒካል አግሪካልቸር፣ ወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ እና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጅኦ ስፓሻል ኢንስቲቱት የተሳተፉ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
የጥናቱ ሂደት የተካሄደው በተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንቬንሽን መስፈርት መሰረት መሆኑንም ገልጸዋል።
መስፈርቶቹ ዛፎች ያረፉበት መሬት ስፋት ከ500 ካሬ ሜትር የማያንስ፣ ቁመታቸው ከሁለት ሜትር የማያንስ እና ቅርንጫፎቻቸው የሚሸፍነው መሬት ከ10 በመቶ የማያንስ መሆን እንዳለበት ያስቀምጣል።
በመስፈርቶቹ መሰረት ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው የደን ሽፋን ልኬት መስፈርት በተባበሩት መንግስታት ድርጀት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንቬንሽን ተቀባይነት ማግኘቱን አስታውሰዋል፡፡
በነዚህ መስፈርቶች መሰረት በተደረገ የደን ሽፋን ልኬት አሁን ላይ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 23 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱን ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
የደን ሽፋኑ ሲሰላ ዘመኑ የደረሰበት ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ትግበራ ጥቅም ላይ መዋሉን ጠቅሰው ከፍተኛ የጂ-አይ-ኤስ እና የሪሞት ሴንሲንግ እውቀት ያላቸው ባለሙያዎች መሳተፋቸውንም ተናግረዋል፡፡