በ 6 ዓመታት ውስጥ ከ1 ሚሊየን በላይ ደንበኞችን ማፍራት ችሏል
(አዲስ አበባ ( ኢትዮጵያ ቱደይ )- የካቲት 29 ቀን 2016 ዓ.ም)
ዳሸን ባንክ ሸሪክ የተሰኘ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የጀመረበትን 6ተኛ አመት ባከበረበት ዕለት ከደንበኞች በበጎ አደራጎት ፈንድ በአደራ የሰበሰበውን 12.5 ሚሊዮን ብር ለ18 አገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ድጋፍ አደረገ፡፡

የካቲት 26 ቀን 2010 ዓ.ም በአንድ መስኮት መስጠት የጀመረው አገልግሎት ፣ አሁን ላይ ከ1 ሚሊየን በላይ ደንበኞችን ማፍራት ችሏል፡፡
የዳሸን ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ በስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ለባንኩ አመኔታቸውን ለሰጡ ደንበኞች ከፍ ያለ ምስጋናቸውን አቅርበው
“ዳሸን ባንክ ወደፊትም ለላቀ ስኬት የሸሪዓህ መርህን በመከተል አዳዲስ የባንክ አገልግሎቶቸን ያቀርባል ሲሉ
የዳሸን ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ ተናግረዋል ።
አቶ አስፋው አክለውም በእለቱ በአደራ የተሰጣቸውን ገንዘብ የተረከቡ 18 አገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጅቶች የማህበረሰቡን ችግር ለመቅረፍ በሚያስችሉ ስራዎች ላይ እንዲያውሉት አደራ ብለዋል፡፡
በቀጣይም ባንኩ እነኚህንም ሆነ መሰል ሌሎች ተቋማት የማህበረሰቡን ችግሮች በዘላቂነት በሚፈቱ ስራዎች ላይ በጋራ ለመስራት የሚሻ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በ ሸሪክ አገልግሎት ከ9.5 ቢሊየን ብር በላይ ማሰባሰብ የቻለ ሲሆን ከዚህም ውስጥ ከ6 ቢሊየን ብር በላይ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ለተሰማሩ ደንበኞቹ ፋይናንስ ማድረጉን ገልጿል ።
ባንኩ እ.ኤ.አ ህዳር 28 ቀን 2023 በባህሬን ማናማ በተካሄደው 9ኛው የኢስላሚክ ሪቴል ባንክ ሽልማት ላይ ጠንካራው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በኢትዮጵያ የሚሰጥ ባንክ (The strongest Islamik Retail Banking Window in Ethiopia 2025) በሚል ተቀማጭነቱ ሎንዶን በሚገኘውና በፋናንስ ዘርፍ ጥናትና ምርምር በሚሰራዉ ኬምብሪጅ አይ ኤፍ ኤ(Cambridge IFA) የተሰኘ ተቋም ሽልማት ማግኘቱን አስታውሷል።
ባንኩ በአለም አቀፍ ደረጃ የእስላማዊ ፋይናንስ ተቋማትን የሂሳብ፣ ኦዲት እና ሸሪዓህ መስፈርቶችን የሚያወጣው ተቋም (AAOIFI) ቋሚ አባል የሆነ በኢትዮጳያ ብቸኛው የፋይናንስ ተቋም መሆኑ ይታወቃል፡፡
ሸሪክ የተለያዮ የተቀማጭ እና ኢንቨስትመንት አማራጮችን ይዞ የቀረበ ሲሆን ለአብነት ወዲዓህ(የአደራ ተቀማጭ ሂሳብ)፣ አን-ኒሰዕ ወዲአህ የሴቶች ሂሳብ፣ የሃጅ መንፈሳዊ ጉዞ ለማከናወን ደንበኞች ቁጠባ የሚያደርጉበት ሃጅ ወዲዓህ የቁጠባ ሂሳብ፣ በዉጭ ሃገር ምንዛሬ የሚከፈት ወዲዓህ የቁጠባ ሂሳብ፣ ቀርድ የተንቀሳቃሽ ሂሳብ (የቼክ ሂሳብ) እና የሙዳረባህ የጊዜ ገደብ ተቀማጭ(የኢንቨስትመንት ሂሳብ) ይገኙበታል፡
አሁን ላይ ከ70 በላይ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በሚሰጡ ቅርንጫፎች እንዲሁም ከ800 በላይ በሆኑ ቅርንጫፎች ደግሞ በመስኮት ለደንበኞቹ የተሟላ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡