አዲስ አበባ (ኢትዮጵያ ቱደይ) የካቲት 29ቀን 2016 ዓ.ም
ከአምስት ዓመታት በፊት ከክልሉ መንግሥት ጋር የሰላም ስምምነት ተፈራርሞ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የተመለሰው የቀድሞው አማጺ ኦብነግ በክልሉ ኦጋዴን አካባቢ የንጹሃን ደም እየፈሰሰ መኾኑን አስታውቋል።
ፖርቲው ይህን ያለው በተረጋገጠ የ”ኤክስ” ገጹ ላይ ባወጣው አጭር መልዕክት ነው።
“ኦጋዴን ውስጥ በሚፈሰው ደም የሚደሰቱ አካላት ይኖራሉ” ያለው ኦብነግ፣ ኾኖም እነዚህ አካላት “አንድ ቀን የእኛ ጊዜ እንደሚመጣ መርሳት የለባቸውም” በማለት አስጠንቅቋል።

ግንባሩ አያይዞም፣ በሕዝባችን ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አካላትን ድርጊት መቼም ቢኾን አንረሳውም ብሏል።
ኦብነግ፣ በክልሉ ሕዝብ ወይም በኦጋዴን አካባቢ ሕዝብ ላይ ጉዳት ያደርሳሉ ወይም ደም ያፈሳሉ ያላቸውን አካላት ማንነት ግን በስም ለይቶ አልጠቀሰም።
ግንባሩ ከሳምንት በፊትም፣ በክልሉ ውስጥ በሲቪል ተሽከርካሪዎች ላይ ይፈጸማሉ ያላቸው “ዒላማ ያልለዩ የመሳሪያ ጥቃቶች” እና “የአርብቶ አደሮችን እንስሳትና ንብረት የመውረስ ድርጊቶች” እንዲቆሙ ጠይቆ ነበር።