አዲስ አበባ (ኢትዮጵያ ቱደይ) የካቲት 20 ቀን 2016 ዓም:- በአማራ እና በትግራይ ክልል በግጭት እና በድርቅ ለተጎዱ አርሶ አደሮች ቢ.ኤ.ኤስ.ኤፍ (BASF) ከኔዘርላንድ የልማት ድርጅት ጋር ሆርቲ ላይፍ (Horti-LIFE) በተባለ ፕሮጀክት 4 ሺህ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች የአትክልት እና የፍራፍሬ ምርጥ ዘር ድጋፍ በግብርና ሚኒስቴር ቅጥር ጊቢ ውስጥ ተካሄደ።
ድጋፉ የኔዘርላንድ የልማት ድርጅት በሆኑ የአርሶ አደሮች የመስክ ማሳያ ትምህርት ቤት ለሚሰለጥኑ አርሶ አደሮች ሲሆን፤ 371 ሄክታር መሸፍን የሚችል 30 ሚሊየን ብር የሚገመት የቲማቲም፣ ቃሪያ፣ የቀይ ሽንኩርት እንዲሁም የሃባብ ምርጥ ዘሮችን ድጋፍ ተደርጓል።
የሆርቲ ላይፍ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አንድነት ባይለየኝ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ድርጅቱ በግብርና፣ ኢነርጂ እና በውሃ ሥራዎች ላይ የተሰማራ ሲሆን ከሚሰራው የግብርና ፕሮጀክት ውስጥ አትክልትና ፍራፍሬ ላይ በሰባት ክልሎች በ147 ወረዳዎች ላይ እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ መለሰ መኮንን በበኩላቸው ድጋፉ በግጭት እና ድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎችን “መልሶ ለማቋቋም እና በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደር ማህበረሰቦች ኑሯቸውን መልሶ የሚያቋቁመበትን እድል ለመፍጠር” ያለመ ነው ብለዋል።
ድጋፉ ለአርሶ አደሮቹ ምርጥ ዘሩን ከመስጠት ባሻገር ከመሬት ዝግጅት እስከ አጠቃላይ ገበያ ድረስ ያለውን ሁኔታ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚደረግላቸውም አዲስ ማለዳ አውቃለች።
ቢ.ኤ.ኤስ.ኤፍ(BASF) በምርጥ ዘር፣ በልዩ ሁኔታ የተመረጡ ዘሮች፣ በስነ ህይወትና ኬሚካላዊ መንገድ የሚደረግ የሰብል ጥበቃ፣ የአፈር አያያዝ መፍትሔዎች፣ የተክል ጤንነት፣ የተባይ ቁጥጥር እና ዲጂታል ግብርና ዘርፍ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል።