በለገሠ ነጋሽ (ፕሮፌሰር)
የአገር በቀል ዛፎች ማለት፣ ልክ እንደ ሕዝቡ ሌሎች እንስሳትና ዕፅዋት ከጥንት ጀምሮ ከኢትዮጵያ የአየር ንብረት፣ ከአፈሩ ኬሚካላዊ ይዘት፣ ከተለያዩ በሽታዎች፣ ከጥቃቅን ህዋሳት፣ እንዲሁም ከልዩ ልዩ ከባቢያዊ ሕይወት ያላቸውና ቁስ አካላዊ ነገሮች ጋር ተላምደው፣ ተጣጥመው፣ የኖሩና የሚኖሩ፣ የብዙ አሠርት ሚሊዮን ዓመታት የሰከነ ለውጥ (Evolution) ውጤቶች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በተለምዶ የአገር በቀል ዛፎች ብለን የምንጠራቸው በሁለት ይከፈላሉ፡፡ አንዳንዶቹ (ለምሳሌ ዝግባ፣ ጥቁር እንጨት፣ ብሳና፣ ወይራ፣ ዋርካና ሾላ ወዘተ) ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ በእንግሊዝኛ Indigenous Trees ተብለው ይጠራሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ (ለምሳሌ እንደ ብርብራና ኮርች ያሉቱ) በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኙ ሲሆኑ በእንግሊዝኛ Endemic Trees ተብለው ይጠራሉ፡፡
የአገር በቀል ዛፎች ምን የተለየ ባህሪና ፋይዳ አላቸው?
ከላይ እንደተጠቀሰው፣ የአገር በቀል ዛፎች የብዙ አሠርት ሚሊዮን ዓመታት የሰከነ ለውጥ ውጤቶች ስለሆኑና ጊዜ ስለፈተናቸው፣ ዘለቄታቸው አስተማማኝ ነው፡፡ ከበሽታው፣ ከድርቁ፣ ከአፈሩ ሁኔታ፣ እንዲሁም ከሌሎች እንስሳትና ጥቃቅን የአፈር ውስጥ ሕዋሳት ጋር ለረዥም ጊዜ ተላምደውና ተጣጥመው የኖሩና የሚኖሩ በመሆናቸው፣ የአገር በቀል ዛፎቻችን ልዩ ሥነ ሕይወታዊ ባህሪን የተላበሱ ናቸው (ፎቶግራፍ 2ን ይመለከቷል)፡፡ ለምሳሌ የፀሐዩ ሙቀት ከዓመት እስከ ዓመት ከፍተኛ፣ በአንፃሩ ደግሞ የዝናቡ መጠን እጅግ ዝቅተኛ በሆነበት በታላቁ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ የግራር ዝርያዎች እጅግ ለምልመውና ተውበት ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ግራሮችና ሌሎች የአገር በቀል ዛፎችና ቁጥቋጦዎች ባይኖሩ ኖሮ፣ ዛሬ ስምጥ ሸለቆው የለየለት በረሃ በሆነ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ ታላቁ ስምጥ ሸለቆ አደጋ አንዣቦበታል፡፡ ለብዙ አሠርታት በተደረጉ ተከታታይ የከሰል ማክሰል ሥራዎች፣ እጅግ ብዙ ውብና የተለያዩ የግራር ዛፎቻችን አልቀው፣ እነሆ ዛሬ በስምጥ ሸለቆውና አካባቢው በረሃማነት እየተስፋፋ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በአስቸኳይ በረሃማነት እየተስፋፋ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ባስቸኳይ ካልተቀለበሰ፣ እየተጠናከረ ከመጣው የአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተዳምሮ ህልውናችንን ከአሁኑ በባሰ ሁኔታ አደጋ ላይ እንደሚጥለው ይተነበያል፡፡
ተመራማሪዎች ምን ይመክሩናል?
በ1936 ዓ.ም. አካባቢ (አብዛኛው የአሁኑ ትውልድ ባልተፈጠረበት ጊዜ ማለት ነው) አንድ የውጭ አገር ተመራማሪና የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ደን ሁኔታ በመጠኑም ቢሆን የዳሰሰ፣ እንዲህ ሲል መክሯል፣ አስጠንቅቋልም፣ ‹‹የኢትዮጵያ መሪዎች ለተፈጥሮ ደኖቻቸው ያላቸውን አመለካከት ካለወጡ በስተቀር፣ ኢትዮጵያ ወደፊት መናጢ ደሃ ትሆናለች፤››
እነሆ ዛሬ ከ70 ዓመታት ‹‹ሥልጣኔና ልማት›› በኋላ የለየልን ‹‹መናጢ ደሃዎች›› ሆነናል፡፡ ከዚህ የድህነት አረንቋ የምንወጣበት አንዱ ብልኃት የአገር በቀል ዛፎችን፣ ቁጥቋጦዎችን፣ ሳሮችንና ቅጠላ ቅጠሎችን መልሰን ስናቋቁማቸው ነው፡፡ የአገር በቀል ዛፎች የእርሻችን መደላሎች፣ የውኃ ሀብት መሠረቶች፣ የባህል መድኃኒት መገኛዎች፣ የስብጥረ ሕይወት ማህፀኖችና በአጠቃላይ የሕልውናችን መሠረቶች ናቸው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
Share