አዲስ አበባ (ኢትዮጵያ ቱደይ) ጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓም
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አንድ ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል ያለዉን የኮንስትራክሽን ግብአት ማምረቻ ፋብሪካ ወደ ምርት ስራ እንዲገባ ማድረጉን አስታዉቋል።
ይህም ለግንባታ ስራ ፍጥነትም ሆነ ጥራት እንዲሁም የዋጋ መጠን ግሽበት ምክንያት ሆኖ የሚጠቀሰው የኮንስትራክሽን ግብአቶችን ወጥ በሆነ ማዕከል ለማምረት እንደሚረዳም ተገልጿል ።
የማምረቻ ማዕከሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አማካሪነት እና በቢኤም ቴክኖሎጂ ተቋራጭነት የማሽኖችን ተከላ፣ የጉድጓድ ውሀ ቁፋሮ፣ የመጋዘን፣ የሼድ ግንባታ፣ ከሁለት ኪ/ሜ በላይ የአጥር እና የቢሮ ግንባታዎች፣ የውስጥ የመንገድ ስራ እንዲከናወን መደረጉን ነዉ ኮርፕሬሽኑ የገለፀው።
የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ረሻድ ከማል በፋብሪካው ምረቃ ወቅት እንደተናገሩት “የዚህ ማምረቻ ማእከል የአርማታ ውህድ ማምረቻው ሁለት የምርት ዩኒቶች ያሉት ሲሆን እያንዳንዳቸው በሰዓት 100 ሜ/ኩብ የማምረት አቅም አላቸው ብለዋል።
እነኚህ ማሽኖች በአመት 202,752 ሜ/ኩብ የአርማታ ውህድ የማምረት አቅም እንዳላቸዉ የገለፁት ዋና ስራ አስፈፃሚው ከዓመታዊ ምርት ሽያጭ ደግሞ ከ 2.29 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢን ማግኘት እንደሚያስችል አስረድተዋል።
ማዕከሉ ኮንክሪት ዉህድ እና ብሎኬት ከማምረት በተጨማሪ የመንገድ ዳር ንጣፍ (ቴራዞ) የሚያመርት በመሆኑ ከኮርፖሬሽኑ ፕሮጀክቶች አልፎ ለሌሎች በመዲናዋ ለሚካሄዱ የግንባታ ፕሮጀክቶች ምርቱን ለማቅረብ ጠቀሜታው የጎላ ነዉ ተብሏል።