በፍክር ጊሊሲ /የፖለቲካ ተንታኝ /
አለም የካቲት 25 ለ26 ምሽት 1992 በአዛርባጃኗ ኮጃሌ ከተማ የተደረገውን አሳዛኙን የኮጃሌ ዘርማጥፋት በሚዘክርበት በዛሬው ዕለት ሙሉ ትኩረታችን እና የጋራ ርምጃችን በእጅጉ ይሻል። እንደ አንቲጋ ካህራማኖቫ ያሉ ከዘር ማጥፋቱ በተዓምር የተረፉት ሰዎች የአርሜኒያ ታጣቂዎች በንጹሃን የአዘርባጃን ዜጎች ላይ ያደረሱትን ጭካኔ በማስታዎስ ያዩትን አሰቃቂ ድርጊት ይመሠክራሉ። እነዚህ ምስክርነቶች ሃቀኛ ፍትህ እንዲሰጥ እና አዛርባጃን ለወደፊት ሰላም ላቀረበችው ጥሪ ዓለም አቀፍ እውቅና እና ድጋፍ እንዲያገኝ እንደ አስታዋሽነት ያገለግላሉ።
የአንቲጋ ምስክርነት በኮጃሌ ህዝብ ላይ የደረሰውን ለማሰብ የሚከብድ ስቃይ ያሳያል። የአርሜኒያ ታጣቂዎች በጭካኔ አስከሬኖችን ሳይቀር ቆራርጠው ጥለዋል። ሰዎችን ከነ ህይወታቸው በእሳት አንድደዋል። በኮጃሌ ህዝብ ላይ በቃላት ሊገለጽ ከሚችለው በላይ መዓት አውርደዋል። በቀድሞው የሶቭዬት 366ኛ ብረት ለበስ በታጀበ የእግረኛ ክፍለ ጦር ሰፊ ድጋፍ ሲደረግላቸው የነበሩት የአርሜኒያ ታጣቂዎች በኮጃሌ ላይ በፈጸሙጥ ጥቃት ሴቶችን፣ ህፃናትን እና አረጋውያንን ጨምሮ 613 ሰዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለዋልል። በተጨማሪም ከ1,275 በላይ ግለሰቦች አግተዋል። ከነዚህ ውስጥ የ150ዎቹ እጣ ፈንታ እስከዛሬ ድረስ አልታወቀም። በአርሜኒያ ሃይሎች የወደመችው የኮጃሌ ከተማም የፍርስራሽ ክምር በማድረግ የሰፊውን ጭፍጨፋ ማስታዎሻ ሆና ነበር።
አዛርባጃን ኮጃሌ ላይ የተካሄደው የዘር ማጥፋት ወንጀል ዓለም አቀፋዊ እውቅና እንዲሰጠው እና ፍትህ እንዲሰፍን ከሦስት አስርተ ዓመታት በላይ ጥሪ ስታቀርብ ቆይታለች። ይሁንና ጥሪዋ ሁሉ ጆሮ ዳባ ልበስ ተብሎ ቆይቷል። በፕረዝዳንት ኢልሃም አልየቭ የምትመራው አዛርባጃን በፈተና እና በችግር ፊት የነበራትን ያላሳለሰ ጽናት እና ቁርጠኝነት ስታሳይ ቆይታለች። እኤአ በ2020 ዓ.ም የመጸው ወራት በተካሄደው የ44 ቀኑ የአርበኝነት ጦርነት እና በመስከረም 2023 ባደረገችው አሸባሪዎችን መልሶ የማጥቃት ርምጃ በህገዎጥ መንገድ የተያዙባትን ግዛቶቿን ሙሉ በሙሉ በማስመለስ የግዛት አንድነቷን ማስጠበቅ ችላለች። በዚህም የጸጥታው ምክር ቤት ያሳለፋቸውን አራት ውሳኔዎች በብርቱ ክንዷ ተፈጻሚ ማድረግ ችላለች። እኤአ ጥቅምት 15 2023 ዓ.ም ላይም የአዛርባጃን ሪፐብሊክ ሰንደቅ ዓላማ በኮጃሌ ከተማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አድርጋለች።
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊት ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የአዛርባጃን ሪፐብሊክ አምባሳደር የሆኑት ሩስላን ናሲቦቭ አዛርባጃን ዜጎቿን መጠበቅ እና የግዛት አንድነቷን በማስቀጠል ሉዓላዊነቷን ማጽናት ላይ ያላትን ቁርጠኝነት በአጽንኦት ይናገራሉ። ሃገራቸው የኮጃሌ ዘር ማጥፋት ወንጀል ሰለባዎችን ስትዘክር ነጻ ባወጣቻቸው ግዛቶቿ ያላትን የአሸናፊነት መንፈስ በማሰብና ከግጭት የጸዳ ወደፊት እንዲኖር ጥረት ማድረግ እንደማታቋርጥ በማስገንዘብ ነው።
የኮጃሊ ሠለባዎች መታሰቢያ አዛርባጃን በዘር ማጥፋት ወንጀሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ ለምታደርገው ፍትህ ለኮጃሌ የተሰኘው ቀጣይነት ያለው ዘመቻ ትልቅ ጠቀሜታ አለው። ወንጀለኞች ተጠያቂ እንዲደረጉ ማስቻል የዘመቻው ተቀዳሚ ዓላማው ነው። ምንም እንኳን ከወንጀለኞቹ መኃል ከገንጣይ አስገንጣይ ተባባሪዎቻቸው ጋርበከፊል በአዛርባጃን የተያዙ እና የፍርድ ቤት ሂደት ውስጥ ያሉ ቢሆንም ዋና ዋና አጥፊዎቹ እስካሁን ከህግ እንደተደበቁ ነው።

የአዛርባጃን የአቋም ጽናት የትላንትናን ቁስል በማገገም ሠላማዊ፣ ፍትህ የሰፈነበትና ብሎም እርቅን መሠረት ያደረገ የወደፊት ዕድል ለመፍጠር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።
አዛርባጃን ተጎጂዎችን በመዘከር፣ በማስተማርና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን በማጠናከር ለፍትህ፣ ዓለም አቀፍ እውቅና እና ለወደፊት ሰላማዊ ህይወት ዘብ ትቆማለች። አዛርባጃን የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለእውነት እንዲቆም ፣ እውቅና እንዲሰጥ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ድጋፍ እንዲያደርግ ለመወትወት ያላት ቁርጠኝነት የለውጥ መሳሪያ በመሆን ያገለግላል። ይህ የፍትህ ድምጽ በዓለም ሲያስተጋባ አዛርባጃንም ለዜጎቿ ብሎም ለመላው ዓለም ህዝብ ሰላማዊ ህይወትን የምትፈልግ ሃገር በመሆን ጸንታ ትኖራለች።
የኮጃሌ የዘር ማጥፋት መታሰቢያ የተፈፀመውን ግፍ በማጋፈጥ፣ ለተጎጂዎች ፍትህን በማረጋገጥ ከሁከት የፀዳ የወደፊት ህይወትን ለማምጣት በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ የሚያሳስብ ነው። ሰላም፣ ፍትህ እና ርህራሄ ለሁሉም ይዳረስ ዘንድ ቁርጠኛ በመሆን እጅ ለእጅ ተያይዘን በአንድነት እንቁም።