አዲስ አበባ ( ኢትዮዽያ ቱደይ) ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም
ከነገ ጥቅምት 6 ቀን 2017 ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ የህዝብ ትራንስፖርት ታሪፍ ላይ ማሻሻያ መደረጉን የከተማዋ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ለተሰማሩ ሚኒ-ባሶች፣ ሚዲ-ባስ ታክሲዎች (ሀይገር ባሶች) እና የከተማ አውቶብሶች ላይ የአገልግሎት ታሪፍ ማሻሻያ አድርጊያለሁ ሲል ገልጿል።
አዲሱ የታሪፍ ማስተካከያው ከነገ ጥቅምት 06 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፤ ቀድሞ አገልግሎት ሲሰጥበት የነበረው የታሪፍ ተመን ከጥቅምት 20/2016 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት ላይ የዋለ እንደነበረና ስሌቱም የነዳጅ ጭማሪ ዋጋን ብቻ ታሳቢ ያደረገ እንደነበር ቢሮው አስታውቋል።
የመዲናዋ የትራንስፖርት ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት ጭማሪ በተደረገበት በአዲሱ ታሪፍ ዝቅተኛው 10 ብር ሲሆን ከፍተኛው 65 ብር ገብቷል።
4 ብር ከ50 ሳንቲም የነበረው 10 ብር፣ 8 ብር ከ50 ሳንቲም የነበረው 15 ብር፣ 13 ብር የነበረው 20 ብር፣ 17 ብር የነበረው 25 ብር፣ 30 ብር የነበረው 40 መሆኑን ቢሮው ካቀረበው ዝርዝር መረጃ ያሳያል።
አሁን የተደረገው የታሪፍ ማሻሻያ ደግሞ ወቅታዊ የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ እና ሌሎች አስተዳደራዊ ወጪዎችን ያማከለ መሆኑን ጠቁሟል።
የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች አዲስ በተሻሻለው ህጋዊ የታሪፍ ተመን ብቻ አገልግሎት እንዲሰጡ ሲል አሳስቧል፤ ይህንን በሚተላለፉት አካላት ላይ ቢሮውና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጥብቅ እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል።