አዲስ አበባ (ኢትዮጵያ ቱደይ) መጋቢት 4 ቀን 2016 ዓ. ም
በግልገል በለስ ከተማ ሁለት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ዉስጥ አንድ የፖሊስ ከፍተኛ መኮንን እና አንድ ወጣት የኮሌጅ ተማሪ፤ በፓዌ ከተማ አንድ ከፍተኛ ጠበቃና የሕግ አማካሪ በጥይት ተመተዉ ተገድለዋል ሲል ፓርቲው በመግለጫው ገልጿል። በተጨማሪም በወምበራ ወረዳ አንድ ባለሀብት በግፍ መገደሉም ገልጿል።
እንዲሁም የካቲት 16 ቀን 2016 በአሶሳ ከተማ አቅራቢያ በሲስተር ትዕግስት ጥላሁን ላይ የተፈጸመዉ ዘግናኝ ጠለፋና የግድያ የወንጀል ድርጊት ተጠርጣርዎች እስከ ዛሬ ድረስ በቁጥጥር ስር አለማዋለቸዉ የዜጎች በሕይወት የመኖር ዋስትና አደጋ ላይ መሆኑን ያመለክታል ሲል ክልላዊ ፓርቲው በልከልን መግለጫ ጠቅሷል።
ባለፉት ስድስት ወራት በከተሞች የቡድን ዝርፊያ፣ ውንብድና፣ ሰዎችን መሰወር፣ ህጻናት ማገትና አሰቃቂ ግድያዎች እየተበራከቱ ቢሆንም አጥፊዎች ለሕግ ቀርበው አስተማሪ እርምጃ እንዳልተወሰደባቸውም ፓርቲው ጠቁሟል።
ይህ ደግሞ በህብረተሰቡ ውስጥ ስጋትና ጥርጣሬ ከመፍጠሩም በላይ በፍትህ ተቋማት ላይ አመኔታ ማጣት እያመጣ መሆኑን አዲስ ማለዳ ከመግለጫው ተረድታለች።
ቦዴፓ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የዜጎችን ሕይወት እየነጠቁ ያሉ ወንጀለኞች ተይዘው ለሕግ እንዲቀርቡ፤ በሕግ ቁጥጥር ስር የዋሉት ደግሞ ተገቢዉን ፍርድ እንዲያገኙ ጠይቋል።
እንዲሁም በመተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ ለሠላም እጅ ያልሰጡ የታጠቁ ኃይሎች ፀብ ጫሪ እንቅስቃሴ አከባቢውን መልሶ ለግጭት የሚጋብዝ በመሆኑ የፀጥታ ኃይሉ ተገቢውን ጥንቃቄ እና እርምጃ እንዲወሰድ ፓርቲው አሳስቧል።
በካማሽ ዞን ሰዳል ወረዳ መነሻቸውን “ከሱዳን ያደረጉ” የተባሉ አካላት በሰላማዊ ዜጎች እና አንድ የፀጥታ አባል ላይ ያደረሱት ግድያ እና አካል ጉዳት አከባቢው ላይ የፀጥታ ስጋት ፈጥሯል ተብሏል።