አዲስ አበባ (ኢትዮጵያ ቱደይ) መጋቢት 3 ቀን 2016 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ በደረሰ የትራፊክ አደጋ ሶስት ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ በ11 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።
ዛሬ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ከ30 ላይ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ልዩ ቦታው ወ/ሮ ቀለመወርቅ ትምህርት ቤት አካባቢ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3፤ 71926 ኦሮ የሆነ ሚኒባስ መኪና ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ ነው አደጋው የደረሰው።

ፖሊስ እንዳስታወቀው መኪናው የጉዞ አቅጣጫውን ከአዲሱ ገበያ ወደ ፒያሳ አድርጎ በመጓዝ ላይ የነበረ ሲሆን ወ/ሮ ቀለመወርቅ ትምህርት ቤት አካባቢ ሲደርስ መንገዱን ስቶ እግረኛ መንገድ ላይ በመውጣት ሁለት እግረኞች ላይ የሞት አደጋ ካደረሰ በኋላ ሌላ የአደጋው ሰለባ ሆስፒታል ከገባ በኋላ ህክምና ላይ ህይወቱ እንዳለፈ ታውቋል።
በአደጋው አሽከርካሪውን ጨምሮ 11 ተሳፋሪዎች ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። የሞት አደጋ የደረሰባቸው 3 ወንዶች ሲሆኑ የ18 እና ሁለቱ የ34 አመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል።