አዲስ አበባ (ኢትዮጵያ ቱደይ) መጋቢት 2 ቀን 2016 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ ከመሬት ልማትና አስተዳደር ጋር ተያይዞ የባለ ጉዳይ እንግልት እና ብልሹ አሰራሮችን የሚያስቀር የዲጂታላይዜሽን ስርዓት በልፅጎ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ እየተሰራ ያለውን የዲጂታላይዜሽን እና የሪፎርም ስራ ተመልክተዋል፡፡
ከንቲባዋ ከምልከታቸው በኋላ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ፤ “በዘርፉ ላይ ያለውን የባለ ጉዳይ እንግልት እና ብልሹ አሰራሮችን የሚያስቀር እንዲሁም ለተገልጋዮች ቀላልና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የዲጂታላይዜሽን ስርዓት አበልፅገን ለአገልግሎት ዝግጁ አድርገናል” ብለዋል፡፡
የዲጂታላይዜሽን ስራው ከማዕከል እስከ ክፍለ ከተሞች ያለውን መሬት በአንድ ማዕከል ለማስተዳደር አቅም የሚፈጥር መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ከንቲባዋ አክለውም፤ ሲስትሙ በየደረጃ ያለውን አገልግሎት ክትትል ለማድረግ እና ለተገልጋዮች ፍትሃዊ እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለን ይሆናል ብለዋል::