ባለድርሻ አካላት ለዚህ ቁርጠኛ መሆን አለባቸው፡፡
በሰለሞን ዜና:- ኢትዮጵያ ቱደይ (የካቲት 25፣ 2016)
በኢትዮጵያ ከ6 አስርት ዓመታት ያለፈ የሠራተኛ ማኅበር የትግል ንቅናቄ ታሪክ ያለው አሁን ባለው የድርጅት የአወቃቀር ቁመናው በሀገር አቀፍ ደረጃ በኮንፌዴሬሽን፤ በኢንዱስትሪ ደረጃ በሙያቸውና በኢኮኖሚያዊው መሠረታቸው በተዋቀሩ በዘጠኙ ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽኖችና በድርጅቶች ደረጃ በመሠረታዊ የሠራተኛ ማኅበራት በተቋቋሙ ከ2200 በላይ አባል በሆኑ ማኅበራት ከአንድ ሚሊዮን አባል ሠራተኞች ያሉት የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበር ኮንፌዴሬሽን በኢትዮጵያ የዝቅተኛ ደመወዝ ወለል መወሰንን በሚመለከት ጊዜው አሁን የመሆኑን ምክንያት ይገልጻል፡፡
አሁን ላይ በመላው የአገሪቱ ክፍሎች በግል በሚተዳደሩ ድርጅቶች ውስጥ ይሠራሉ ተብሎ ከሚገምተው ከአራት ሚሊዮን የሚበልጡ ሠራተኞችንና በመንግሥት ሲቪል ሰርቪስ መ/ቤቶች ተቀጥረው የሚሠሩትን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ8 ሚሊዮን ያላነሱ ሠራተኞች እየሠሩ መሆኑን የሚያምነው ኢሠማኮ በተለይ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ተቀጥረው የሚገኙ ሠራተኞች አብዛኞቹ የሚከፈላቸው ከ1000 ብር የማይበልጥ ክፍያ አሁን በተጨባጭ እየታየ ካለው የኑሮ ውድነትና ለመኖር የሚጠይቀውን ክፍያ በማንጻጸር እጅግ ከልክ ያነስ ዝቅተኛ ክፍያ መሆኑንና ሊሻሻል ይገባል ብሎ ያምናል፡፡
አብዛኛው ሠራተኛ ምሳ በልቶ እራት ለመደገም የማይችል ነው፡፡ አንድ ሺህ ብር በኢትዮጵያ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ገበያ ተወጥቶ ምንም አይገዛም፡፡ እንኳን ለወር ይቅርና ለቀናት የሚያቆይ አይደለም፡፡ እንደ የኢሠማኮ ፕሬዝዳንት አቶ ካሣሁን ፎሎ “ለሠራተኛ የሚከፈለው እጅግ ያነስ ደመወዝ ተመጣጣኝ ያልሆነና ለዓመታት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል (minimum wage) በሀገሪቱ ተግባራዊ እንዲሆን፣መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶየደመወዝ ወለል እንዲወሰን ሲወተወት ቆይቷል፡፡”
ኢሠማኮ የዝቅተኛ ደመወዝ ጉዳይ በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲካተት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ጠንክሮ በመሥራቱ ኢትዮጵያ ለዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ሥርዓት መዘርጋት በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ለመጀመሪያ ጊዜ እውቅና ሠጥታለች፡፡ ለዚሁ ሕጋዊ ድንጋጌ ማስፈፀሚያ የአገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት፣ የሥራ ገበያ ሁኔታ የመሳሰሉትን እያስጠና ዝቅተኛ የደመወዝ ክፍያ የሚወስን የመንግሥት፣ የአሠሪና የሠራተኞች ተወካይ፣ እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚሣተፉበት የደመወዝ ቦርድ ስለሚቋቋምበትና ተግባርና ኃላፊነቱ ስለሚወሰንበት ሁኔታ የሚኒስትሮች ም/ቤት ደምብ እንዲያወጣም በአዋጁ አንቀጽ 55 (2) ተደንግጓል፡፡
አዋጁ ኢትዮጵያ ተቀብላ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና የሌሎች አገሮች ተሞክሮዎች ተፈትሸው፣ አገሪቱ እየተከተለቻቸው ያሉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተዳሰው፣ አገሪቱ ያለችበት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ የዕድገት ደረጃ ተጠንተው፣ በአጠቃላይ ሕጉ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታና እያስመዘገበች ካለው ዕድገት አንጻር አብረው እየታየ ያሉ ለውጦች ጋር ተጣጥሞ የሚሄድ እንዲሆን ለማስቻል፣ ከሚመለከታቸው የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆነ ባለድርሻ አካላት ማለትም ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ ከኢትዮጵያ አሠሪዎች ማኅበር ኮንፌዴሬሽን፣ ከኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽኖች ኮንፌዴሬሽን፣ ከጠቅላይ አቃቤ ሕግ ከተለያዩ የፌዴዴራልና የክልል አስፈጻሚ አካላት ጋር የጋራና የተናጠል ውይይት ተደርጎበት የአዋጅ ማሻሻያ አስፈላጊነቱና ወቅታዊነት ስለታመነበት የጋራ መግባባት የተደረሰባቸው የማሻሻያ ሀሣቦች ተገናዝበው በአገሪቱ ሕግ- አውጪ የጸደቅ ነው፡፡
ሁለተኛ፣ በዚሁ የአገሪቱ የሕግ ድንጋጌ ላይ ተመሥርቶ፣ ከፍተኛ የሦስትዮሽ አካል በቢሾፍቱ ከተማ ከሜይ 14-15፣ 2019 ባካሄደው ቴክኒካዊ ስብሰባ፣ ሜይ 16፣ 2019 በኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው የዝቅተኛ ወለል ደመውዝ ሥርዓት መዘርጊያና የደመወዝ ቦርድ ማቋቋሚያ ፍኖተ-ካርታ አጽድቋል፡፡ ያ ከፍተኛ የሦስትዮሽ ስብሰባና ቴክኒካዊ ውይይት ተዘጋጅቶ የነበረው በዓለም ሥራ ድርጅት የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ፣ በቀድሞው የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሲሆን፣ ተሣታፊዎቹም – የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ከአዲስ አበባ፣ ከአፋር፣ ከአማራ፣ ከቤኒሻንጉል፣ ከጋምቤላ፣ ከኦሮሚያ እና ከደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረ-ሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቢሮዎች፤ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን፤ ከኢሠማኮ፣ ከኢትዮጵያ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን፤ ከኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን እና ከኢትዮጵያ አበባ አምራቾች ማሕበር የተውጣጡ ነበሩ፡፡ ተሣታፊዎቹም የሚከተሉትን ተጨባጭ ሁኔታዎች፣ መልካም ዕድሎችና ተግዳሮቶች ለይተው፤ ከተወያዩ በኋላ፣ በፍኖተ-ካርታው ማጠቃለያ ለመንግሥት ጥሪ አድርገዋል፡፡
በሶስትዮሽ ስብሰባው አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ኢትዮጵያ በሁለንተናዊ መልክ ራሷን እየለወጠች ያለች፣ ኢንዱስትሪያዊ ጉዞ እንደጀመረችና የማምረቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮችንና የአግሮ-ፐሮሰሲንግ የልማት መዋቅሮችን እየገነባች መሆኗን መገንዘባቸውን፣፤በኢትዮጵያ በሚደረጉ ልማታዊ ጥረቶች ምርታማነትንና ተወዳዳሪነትን የሚጨምር የሥራ ፈጠራና ምቹ ሥራ ቁልፍ ቅድምና የተሰጣቸው መሆኑን ማስተዋላቸውን፣ኢትዮጵያ በ2025 መካከለኛ ገቢ ያላት ሀገር እንድትሆን የተነደፈው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድና ራዕይ ለአካታችና በምቹ ሥራ ለበለፀገ ዕድገት የጀርባ-አጥንት መሆኑን መገንዘባቸውን፤ብዙ ሠራተኞች ስለዝቅተኛ ደመወዝ ለሚያቀርቡት ቅሬታ፤ ይህም በአንዳንድ ሴክተሮች ለከፍተኛ ሥራ መልቀቅ፣ ለከፍተኛ የሥልጠናና የክህሎት ማሳደጊያ ወጪ፣ ከሥራ መቅረት፣ ለዝቅተኛ ምርታማነትና የሥራ ዕድል እጦት የሚኖረው አስተዋጽኦ ትኩረት የሚያሻው መሆኑን አጽንዖት ሰጥተው ፤ተሣታፊዎቹ፣ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ሠራተኞችን ለመከላከል፣ የሠራተኞችንና ቤተሰቦቻቸውን ሰብአዊ ክብር የመጠነ የኑሮ ደረጃ ለማረጋገጥ፣ ለከፍተኛ ምርታማነት አስተዋጽዖ ለማበርከት፣ ፍጆታን ለማነቃቃት እና የኢንዱስትሪ ሠላም ለማረጋገጥ አስፈላጊ መሣሪያ መሆኑ ላይ ተስማምተዋል፡፡
በወቅቱ ይታይ የነበረው የሦስትዮች ሸሪኮች ቁርጠኝነት፤የዝቅተኛ ደመወዝ ቦርድ ለማቋቋም በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ የተፈጠረው ደጋፊ የሕግ ማዕቀፍ፤የሀገሪቱን የዕድገት ደረጃ፣ ተወዳዳሪነት እና የመክፈል አቅም፤ እያደገ የመጣውን የምርትና አገልግሎት ተጠቃሚዎች፣ የበርካታ ሠራተኞችና፣ አሠሪዎች ጥያቄዎችን ግምት ውስጥ ያስገባ፤ ለዝቅተኛ ደመወዝ ወለል መወሰኛ ሥርዓት መመሥረት እውቅና የሰጠ ብሔራዊ የሥራ ሥምሪትና ስተራቴጂ ፖሊሲ መነደፉ፤ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና ኢንደስትሪያላይዜሽን የመልካም እድሎች(opportunities)ተደርገው የተወሰዱ ተወስደዋል፡፡
ኢሠማኮ አዋጁ ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ፣ ደንቡ በሚኒስትሮች ም/ቤት እንዲጸድቅ ጥረቱን በመቀጠል የኢትዮጵያ ሠራተኞች አሁን እያጋጠማቸው ባሉት ችግሮች ላይ ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን በመመልከት ጥያቄውን ወደ ጠ/ሚኒስትሩ፣ ወደ ፋይናንስ ሚኒስቴር ከመውሰዱም በተጨማሪ ለፓርላማው የሰው ሀብት ቋሚ ኮሚቴም ጉዳዩን በማንሳት በዝቅተኛ የደመወዝ ወለልና ከግብር ጋር የተያዩዙ ጉዳዮች ላይ በመወያያት መፍትሄዎችን ለማግኘትና አጃንዳውን ወደፊት ለማራመድ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር ለመወያየት ቃል እንደተገባለትም ገልጾአል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ(ዶ/ር) በጽ/ቤታቸው ለኢሠማኮ ሥራ አስፈጻሚዎች አቀባበል አድርገውላቸው የዝቅተኛ ደመወዝ ክፍያን ጨምሮ የግብር ማሻሻያ፣ በመደራጀትና የመደራደር መብት ዙሪያ እንዲሁም ተቋሙ ባነሳቸው ሌሎች ችግሮች ዙሪያ ተወያይተው እንደሚታሰብባቸውንና በጊዜው እንደሚፈቱ አረጋግጠውላቸዋል፡፡
የዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ሥርዓትን ለመዘርጋት በሚደረገው ጥረት “የሥራ ፈጠራን፣ ኢንቨስትመንትና የኑሮ -ንረትን “ያወሳስባል፤ ወደ ሥራ እጦት ሊመራ ይችላል የሚል አደናቃፊ ሀሣብ ስለማይጠፋና አወሳሰኑን በሚቋወሙ ኃይሎች በተለያዩ ሀገሮች ሲነሳ ከተለያዩ ሀገራት ተሞክሮ የተስተዋለ መሆኑን በመገንዘብ በተለያዩ ሀገራት ተጨባጭ ልምዶች የተረጋገጠውን ግን፣ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ሥርዓት ከሌሎች ለሥራ ፈጠራ፣ ለኢንቨስትመንትና ለኑሮ-ንረት አወሳሳቢ ከሆኑት በርካታ ቅድመ ሁኔታዎች የበለጠ ምክንያት አለመሆኑን፣ ይህ በኢትዮጵያ ግንዛቤ ውስጥም ገብቶ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡
ዝቅተኛ ደመወዝ መወሠን ሠራተኞችን ብቻ ሣይሆን አሠሪንና መንግሥትንም የሚጠቅም ነው፡፡ ሠራተኞች በሚገባ ካልተመገቡ አሠሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ መጠበቅ አይቻሉም፡፡ በተጨማሪም በሥራ ቦታ አደጋዎትን ውጤትን ይከላከላል፡፡ የሙያ ደህንነትና ጤንነትን ያበረታታል፡፡ ተመጣጣኝ ደመወዝ ያላቸው ሠራተኞች በሙሉ በሥራቸው ያተኩራሉ፡፡ለሥራቸው ተገቢ ክፍያ ካልተከፈላቸው የኑሮአቸውን ጭንቀት ወደ ሥራቸው ይዘው እንዲመጡ ስለሚያደርጋቸው በሚሠሩባቸው ማሽነሪዎችና ኬሚካሎች ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል፡፡ይህ ደግሞ አሠሪውን ላልታቀደ ከፍተኛ ወጪ ይዳርገዋል፡፡በመሆኑም በኢትዮጵያ ካሉ አሠሪዎችም ሆነ ኢንቨስትሮች ጋር ለረጅም ጊዜ ውይይት በመደረጉ ጉዳዩን ያውቁታል፡፡ እንዲያውም እነርሱም የሚፈልጉት በመሆኑ በኢትዮጵያ የደመወዝ ወለል መቼ እንደሚወሰን እየጠየቁ ነው፡፡
ዝቀተኛ የደመወዝ ወለል በአግባቡ ከተነደፈ (well- designed) ፤ ሠራተኛውን ተገቢ ካልሆነ ዝቅተኛ ክፍያ እና ብዝበዛ በመከላከል፤ ትክክለኛና ፍትሃዊ የዕድገት ፍሬዎች ክፍፍል ለሁሉም እንዲደረስ በማረጋገጥ፣ ድህንነትን በመቀነስ፣ መበላለጥን (በሴቶችና ወንዶች መካከል ያለውን ጨምሮ) በማጥበብ፤ ለእኩል ሥራ የእኩል ክፍያ መብትን እውን በማድረግ እና ለክፍያዎች በሕግ መሠረት የተወሰነ ወለል በመዘርጋት ረገድ አስተዋጽኦ እንዳለው በዓለም ዙሪያ ከታየው ልምድ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
በተጨማሪም፣ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ሥርዓት መዘርጋት ድህንነት በመቀነስ፣ መበላለጥን በማጥበብ እና ለሁሉም ሴቶችም ወንዶች ምቹ ሥራን በማስፈን ረገድ ከተባበሩት መንግሥታ ቀጣይነት ያለው የልማት አጃንዳ ግብ 8 እና 10 ጋር ተያያዥነት ያለው በመሆኑ፣ አካታች ፣ ምርታማ የሥራ ሥምሪትና ቀጣይ ዕድገትና ልማት አስተዋጽኦው የላቀ መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡
አሁን ምን መደረግ ይኖርበታል? ብለን ከጠየቅን የዝቅተኛ ደመወዝ ወለል ቦርድ በተቻለ በፍጥነት ተቋቁሞ ዝቅተኛ ደመወዝ እንዴት እንደሚወሰን ጥረት ሊደረግ ይገባል፡፡ አንዳንዶች አዋጁ ሊሻሻልና ዝቅተኛ የደመወዝ ክፍያ መወሰኑ አስፈላጊ መሆኑን ወይም አለመሆኑን ለማወቅ ጥናት መደረግ አለበት እያሉ ነው፡፡ አሁን ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን የመወሰን አስፈላጊነትን በሚመለከት አጃንዳው ተዝግቷል፡፡ በአስፈላጊነቱም ሁሉም ተስማምቶ በሕጉ እንዲካተት ተደርጓል፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ጥናቱን የሚከታተል ቦርድ ማቋቋም አለበት፡፡ ሠራተኞች እና አሠሪዎች ዝቅተኛ የደመወዝ መጠንን መወሰንን አስፈላጊ እና ወቅታዊ ለሁሉቱም ወገኖች እና ለመንግሥትም ጭምር የጋራ ጥቅም መሆኑን አስቀደመው ተረድተዋል፡፡
በዚህም በኢንዱስትሪዎና የሙያ መስኮች የተሰማሩ ሁሉም ዝቅተኛ ተከፋይ ሠራተኞችን የሚሸፈንና አግላይነትን የሚቀንስ ሥርዓት ማቆም፣ የኢኮኖሚውን ሁኔታዎች ግምት ውስጥ ያስገባ፣ የሠራተኛውንና ቤተሰቡን መሠረታዊ ፍላጎቶች የሚሸፍን እንደ ሁኔታው ማስተካከያ የሚደረግበት ፍትሃዊ የዝቅተኛ የደመወዝ ወለል መትከል፣ እነዚህ ሁሉ በተሟላ፣ ውጤታማና ትርጉም ባለው የማኅበራዊ ሽሪኮች ማኅበራዊ ምክከር የተማከሉ እንዲሆኑ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡
በአግባቢ የተነደፈ የደመወዝ ወለል የሚኖረውን አስተዋጽኦ ስናወሳ፣ ለከፍተኛ ምርታማነት አስተዋጽኦ ለማበርከት፣ ፍጆታን ለማነቃቃት እና የኢንዱስትሪ ሠላም ለማረጋገጥ አስፈላጊ መሣሪያ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡