አዲስ አበባ (ኢትዮጵያ ቱደይ) የካቲት 20 ቀን 2016፣ ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በተካሄደበት ወቅት ምርጫ ሳይደረግ በቀረባቸው ቦታዎች፤ በመጪው ሰኔ ወር መጀመሪያ ምርጫ ሊካሄድ ነው። ምርጫ የሚደረገው፤ በአራት ክልሎች ውስጥ ለሚገኙ ዘጠኝ የፓርላማ መቀመጫዎች እና 26 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህንኑ የተመለከተ የጊዜ ሰሌዳ፤ ዛሬ አርብ የካቲት 22፤ 2016 የፖለቲካ ፓርቲ እና የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች በተገኙበት ይፋ አድርጓል። በጊዜ ሰሌዳው መሰረት ምርጫው በሚካሄድባቸው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋር፣ ሶማሌ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ባሉ የምርጫ ክልሎች፤ መራጮች ድምጽ የሚሰጡት ሰኔ 6፤ 2016 ዓ.ም. ይሆናል።
ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫውን ለማካሄድ፤ 1,146 የምርጫ ጣቢያዎች እንደሚቋቋሙ በዛሬው መርሃ ግብር ላይ ተጠቅሷል። ከእነዚህ የምርጫ ጣቢያዎች መካከል ሰላሳ አራቱ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው ቦታዎች የሚቋቋሙ መሆኑን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል። በአሁኑ ወቅት የጸጥታ ችግር በሌለባቸው ቦታዎች ይካሄዳል በተባለው በዚሁ ምርጫ፤ የመራጮች ምዝገባ የሚከናወነው ከሚያዝያ 7 እስከ 21፤ 2016 ባሉት ጊዜያት እንደሚሆንም ቦርዱ ገልጿል ።