አዲስ አበባ (ኢትዮጵያ ቱደይ) የካቲት 18 ቀን 2016 ፣ የካቲት 17 ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ይህ ዘገባ እስወጣበት ወቅት ድረስ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የ21 ሰዎች ህይወት በትራፊክ አደጋ ሲያልፍ በ25 ሰዎች ላይ ከባድ እንዲሁም በ8 ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት መድረሱ ማወቅ ተችሏል፡፡
ከተለያዩ ምንጮች ባሰባሰበችው መረጃ በወላይታ ዞን፣ በምስራቅ ጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ እንዲሁም ዱከም አካባቢዎች የተከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች ባለፉት ቀናት በርካቶችን ገድሎ ሌሎችንም ለጉዳት ዳርጓል።
ከአርባምንጭ ከተማ ወደ ሐዋሳ ከተማ በመጓዝ ላይ የነበረ ተሽከርካሪ በወላይታ ዞን ውስጥ የመገልበት አደጋ እንደደረሰበት ተጠቁሟል። በምስራቅ ጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ ደግሞ ከአዲስ አበባ ወደ ቡታጅራ ይጓዝ የነበረ ተሳቢ ከባድ ተሽከርካሪ ሰባት ሰዎችን ካሳፈረ ባለሶስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) ጋር ተጋጭቶ የሰዎች ህይወት አልፏል።
በቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ዱከም ክፍለ ከተማ ኮድ 2 የሆነ ሬንጅ ሮቨር ተሸከርካሪ ከመንደር ውስጥ ወደ ዋና አስፋልት በፍጥነት ሲወጣ በዋና መንገድ ላይ ከገላን ወደ ዱከም ይጓዝ ከነበረ ሲኖትራክ ተሸከርካሪ ጋር ተጋጭተው አደጋ ደርሷል።